በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ምላሽ ሥርዓትን ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግ ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው - የጤና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ምላሽ ሥርዓትን ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግ ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው - የጤና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ሰኔ 6/2015(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ምላሽ ሥርዓትን ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግ ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ፡፡
በኢትዮጵያ ለአምስት ዓመታት የሚተገበር የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ምላሽ ፕሮጀክት ይፋ ተደርጓል፡፡
ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ምላሽ ሥርዓትን እና በሽታ የመከላከል አቅምን ለመገንባት የሚያስችል ነው ተብሏል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በዚሁ ወቅት፤ ለፕሮጀክቱ የአሜሪካ የተራድኦ ድርጅት/ዩ ኤስ አይ ዲ/ የ12 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡
ፕሮጀክቱን የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር እና የማኔጅመንት ሳይንስ ፎር ሄልዝ የተባሉ ድርጅቶች ከጤና ሚኒስቴር እና ከኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ተግባራዊ እንደሚያደርጉትም ተናግረዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በኦሮሚያ፣ በደቡብ እና በአማራ ክልሎች በተመረጡ 12 ወረዳዎች እንዲሁም በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር እንደሚተገበርም ጠቅሰዋል፡፡
በፕሮጀክቱ አማካኝነትም የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ምላሽ ሥርዓት የልህቀት ማዕከላት ማቋቋም እና በወረዳ ደረጃ ያለውን የጤና ዝግጁነትን የማሻሻል ሥራ እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡
በሌላ መልኩ ወረርሽኞች እንዳይከሰቱ መከላከል፣ ተከስተው ሲገኙም ቶሎ በመለየት ፈጣን ምላሽ የመስጠት አቅምን እንደሚያግዝ ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮጵያ የማይበገር የጤና ሥርዓት ከመፍጠር እንዲሁም ሕብረተሰቡን ከድንገተኛ የጤና ችግሮች ለመጠበቅ መንግሥት ከሚሰራው ሥራ በተጓዳኝ የአጋር ድርጅቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በጤና ዙሪያ የሚሰሩ ሥራዎች ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡
የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ሚሽን ዳይሬክተር ቲሞቲ ስቴን በበኩላቸው፤ የተራድኦ ድርጅቱ ለኢትዮጵያ የጤና ሴክተር በዓመት 200 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በሙከራ ደረጃ ከሚተገበርባቸው አካባቢዎች በተጨማሪ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንደሚሰፋም አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ዋና ጸሐፊ ጌታቸው ታአ፤ ማኅበሩ በፕሮጀክቱ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እንደሚያግዝ አውስተዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ተግባራዊ የሚሆንባቸው ወረዳዎች የተመረጡት ባላቸው የበሽታ ተጋላጭነት፣ ከዚህ በፊት በተደረጉ የጤና ሪፖርቶች እና ሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
በፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ላይ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ፣ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት/ዩ ኤስ አይ ዲ/ ሚሽን ዳይሬክተር ቲሞቲ ስቴን፣ በኢትዮጵያ የቀይ መስቀል ማኅበር የሥራ ኃላፊዎች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡