ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ እና በህንድ መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ይሰራል--አምባሳደር ደመቀ አጥናፉ

አዲስ አበባ ሰኔ 6/2015(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ እና በህንድ መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሰሩ በህንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ደመቀ አጥናፉ ገልጹ።

አምባሳደር ደመቀ አጥናፉ የሹመት ደብዳቤያቸውን ቅጂ ለህንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፕሮቶኮል ሃላፊ አንሹማን ጓር አቅርበዋል።

በወቅቱም በሁለቱ የስራ ሃላፊዎች መካከል በኢትዮጵያ እና በህንድ መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ተደርጓል።


 

አምባሳደር ደመቀ በኢትዮጵያ እና በህንድ መካከል ታሪካዊ የሆነ ግንኙነት መኖሩን አስታውሰው ኢትዮጵያ ግንኙነቱን ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላት ተናግረዋል።

አምባሳደሩ በህንድ በሚኖራቸው ቆይታም የሀገራቱ ግንኙነት በተለይ በፖለቲካ፣ በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና አቅም ግንባታ ዘርፎች እንዲጠናከር ትኩረት አድርገው እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

በህንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፕሮቶኮል ሃላፊ አንሹማን ጓር በበኩላቸው በኢትዮጵያ እና በህንድ መካከል ያለው ታሪካዊ ግንኙነት በአምባሳደር ደመቀ የቆይታ ግዜ ይበልጥ እንደሚጠናከር ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ለሁለቱ ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነትና ለሁለትዮሽ ግንኙነት መጠናከር የህንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚጠበቅበትን ድጋፍ እንደሚያደርግም ቃል መግባታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም