ቀጥታ፡

ባለፉት አስራ አንድ ወራት  ወደ ውጭ ከተላከ ቡና ከ 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር  በላይ ገቢ ተገኘ

አዲስ አበባ ሰኔ 06/2015 (ኢዜአ)፡- በበጀት ዓመቱ ባለፉት አስራ አንድ ወራት ወደ ውጭ ከተላከ 210 ሺህ ቶን ቡና  ከ 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ ለኢዜአ እንዳሉት በአለም አቀፍ ገበያ የቡና ግብይት ዋጋ እየቀነሰ ቢመጣም የኢትዮጵያ ቡና ተፈላጊነቱ እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል። 

ሀገራት በተለያዩ ምክንያቶች ቡና የመግዛት አቅማቸው መዳከሙን ተከትሎ በአለም አቀፍ ገበያ የቡና ዋጋ 30 በመቶ መውረዱን ነው ዋና ዳይሬክተሩ ያብራሩት ።

አለም አቀፍ ግጭቶች የችግሩ መሰረት ቢሆኑም ኢትዮጵያ የገበያ መዳረሻዎቿን በማስፋት በቡና ወጪ ንግድ የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገቧን ጠቅሰዋል። 

በዚህም በዘንድሮው በጀት ዓመት ባለፉት 11 ወራት 210  ሺህ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከ 1 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር በላይ  ገቢ መገኘቱን ተናግረዋል።

ከእቅዱ አንፃር ለውጭ ገበያ የቀረበው ምርትና የተገኘው ገቢ በተወሰነ መጠን ቅናሽ ቢያሳይም ከችግሩ አንፃር የተገኘው ውጤት ጥሩ መሆኑንም ተናግረዋል።

በተያዘው ወር ተጨማሪ ምርት ወደ ውጭ በመላክ አፈጻጸሙ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ለማቀራረብና ጥራትን መሰረት አድርጎ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

እንደ ዳሬክተሩ ገለጻ በቀጣይ በጀት ዓመት ጥራትን መሰረት ያደረገ ስራ በመስራትና የገበያ መዳረሻዎችን በማስፋት የተሻለ ገቢ ለማግኘት በርካታ ስራዎች እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።

በተለይ ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ፣ጥራትን የማስጠበቅ፣ ግብይቱን የማዘመንና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል። 

በ2014 በጀት አመት  300 ሺህ ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱ ይታወቃል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም