በግጭት ምክንያት የወደሙ መሠረተ-ልማቶችን መልሶ ለመገንባትና ለማቋቋም የተባበረ ጥረት ያስፈልጋል - የክልል ርዕሳነ-መስተዳድሮች - ኢዜአ አማርኛ
በግጭት ምክንያት የወደሙ መሠረተ-ልማቶችን መልሶ ለመገንባትና ለማቋቋም የተባበረ ጥረት ያስፈልጋል - የክልል ርዕሳነ-መስተዳድሮች
አዲስ አበባ ሰኔ 6/2015(ኢዜአ)፦በግጭት ምክንያት የወደሙ የመሠረተ-ልማት አውታሮችን መልሶ ለመገንባትና ለማቋቋም የተባበረ ጥረት እንደሚያስፈልግ የክልል ርዕሳነ-መስተዳድሮች ገለጹ።
የኢትዮጵያ መልሶ ማቋቋም እና መገንባት የጥናት ውጤት ላይ ትኩረት ያደረገ የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በመድረኩም ግጭት የተከሰተባቸውን አካባቢዎች ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ለመልሶ ማቋቋም ግንባታ ፕሮግራም የሚውል የ20 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር መርሃ-ግብር ይፋ ሆኗል።
የዳሰሳ ጥናት በሸፈናቸው ክልሎች በማኅበራዊ፣ በምርት፣ በመሠረተ-ልማት እና ባለብዙ ዘርፎች አጠቃላይ 22 ነጥብ 69 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ውድመት መድረሱም ተጠቁሟል።
የምክክር መድረኩ ዓላማ በተለያዩ ግጭቶች የደረሰውን ጉዳትና መልሶ ማቋቋም የፍላጎት ዳሰሳ ጥናት ላይ ምክክር በማድረግ ሰው ተኮር ልማትን በማጠናከር ግንኙነትን ለማደስ እንደሆነ ተገልጿል።
የአማራ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ጦርነቱ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በሚሰጡ ተቋማትና መሠረተ-ልማቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አስከትሎ አልፏል፡፡
በጦርነቱ የደረሰውን የውድመትና የኪሳራ መጠን ለመለየትም ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ጥናት ተካሂዶ ውጤቱ ይፋ መደረጉን ተናግረዋል።
የክልሉ መንግሥት ከፌደራል መንግሥትና ከልማት ድርጅቶች ጋር በመተባበር በመልሶ ግንባታና ማቋቋም ሥራ በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝ አንስተዋል።
በጦርነቱ የደረሰውን ከፍተኛ ውደመትና ኪሳራ በዘላቂነት ለመገንባትም የልማት አጋር ድርጅቶችና ተቋማት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
በተመሳሳይ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ-መስተዳድር ጌታቸው ረዳ፤ ጦርነቱ በመሠረተ-ልማት እና የሕዝብ መገልገያ ተቋማት ላይ ከፍተኛ ውድመት በማስከተል ሰብዓዊ ቀውስ ማድረሱን ተናግረዋል።
በጦርነት የተጎዱ ክልሎች ካጋጠማቸው የመሠረተ-ልማት ውድመት በመውጣት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የልማት ሥራዎች እንዲያከናውኑ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፉን እንዲያስቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ፤ በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠረ ግጭት በጤና፣ በትምህርትና ሌሎች የመሠረተ-ልማት ተቋማት ላይ ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል።
ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ የመልሶ ግንባታ ፕሮግራሙም የደረሰውን ጉዳት መልሶ ለመገንባት ያግዛል ብለዋል።
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አሻድሊ ሐሰን፤ በክልሉ የተፈጠሩ ግጭቶች በመሠረተ-ልማት ውድመት በዜጎች ደግሞ መፈናቀልና የህይወት መስዋዕትነት ማስከተሉን ተናግረዋል።
በትምህርት እና ጤና ተቋማት ላይ የደረሰውን ውድመት መልሶ ለመገንባትም የልማት አጋሮች ትብብር አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የዓለም ባንክ፣ በተመድ የልማት ፕሮግራም፣ የአውሮፓ ሕብረት እና ሌሎች አጋር የልማት ተቋማት ኢትዮጵያ ለምታካሂደው የመልሶ ግንባታ ሥራ የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።
መንግሥት በዓለም ባንክ እና በልማት አጋሮች የቴክኒክ ድጋፍ ግጭቱ ያደረሰውን ውድመት፣ ጥፋት እና የፈጠረውን ፍላጎት አካታች መረጃ ለመስጠት የጉዳት ፍላጎት ግምገማ ማድረጉም ተመላክቷል።