ቀጥታ፡

የአክሱም ሀውልት ዳግም ለጎብኚዎች ክፍት ሆነ

አክሱም፣ ሰኔ 06/2015 (ኢዜአ) የአክሱም ሀውልት ዳግም ለጎብኚዎች ክፍት መደረጉን የአክሱም ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የአክሱም ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ሀላፊ አቶ ገብረመድህን ፍፁም ብርሀን ለኢዜአ እንዳስታወቁት፤ በአክሱም ከተማና አካባቢው የሚገኙ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ጥንታዊ ቅርሶች ለቱሪስቶች ክፍት ተደርገዋል።

ቅርሶቹ ዳግም ለጎብኚዎች ክፍት እንዲሆኑ ሕብረተሰቡ በጉልበቱ፣ በገንዘቡና በሙያው ያደረገው ተሳትፎ የላቀ እንደነበረም ተናግረዋል።

የቱሪዝሙን ዘርፍ ወደነበረበት ለመመለስና ሕብረተሰቡ ለቱሪስቶች የሚሰጠውን አገልግሎት ለማሳደግ ለፎቶ አንሺዎች፣ አስተርጓሚዎች፣ ለባህላዊ ጌጣጌጦችና ቅርፃቅርፅ ባለሙያዎች እንዲሁም ለባለ ሆቴሎች ስልጠና መሰጠቱን አሰረድተዋል።

በአክሱምና አካባቢው የሚገኙ ቅርሶችና ሙዚየም ለቱሪስቶች ተደራሽ ለማድረግ ከዛሬ ጀምሮ ክፍት መደረጋቸውን ገልጸዋል።

በአክሱምና አካባቢው የሚገኙ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ጥንታዊ ቅርሶች ለመጎብኘትና ለማየት በየአመቱ ከ30 ሺህ በላይ የውጭ ሃገር ቱሪስቶች ይጎበኙት እንደነበር አስታውሰዋል።

ጎብኝዎቹ በአክሱምና አካባቢ በሚኖራቸው ከ2 እስከ 3 ቀናት ቆይታ ከሚያገኙት አገልግሎት የቱሪዝም ጽህፈት ቤቱና ነዋሪው በዓመት ከ180 ሚልዮን ብር በላይ ገቢ ያገኝ እንደነበረም ጠቅሰዋል።

በባህላዊ ቅርጻ ቅርፅ ዘርፍ ተሰማርቶ ኑሮውን ሲደጉም የነበረው ወጣት እዝግነአምን ኪዳነ፣ ከነቤተሰቦቹ ለከፍተኛ ችግር ተጋልጦ መቆየቱን ገልጸዋል።

ወጣቱ በተፈጠረው ሰላም የቱሪዝሙ ዘርፍ እንቅስቃሴ መጀመሩ የሚሰራውን የቅርፃ ቅርጽ ስራ አጠናክሮ በመቀጠል የራሱንና የቤተሰቡን ኑሮ ለማሻሻል እንደሚተጋ አብራርቷል።

በሰፌድና አለላ ስራ ተሰማርታ ከጎብኚዎች ገቢ ታገኝ የነበረችው ወጣት አዜብ አሰፋ፣ በሰላሙ ወቅት በዓመት እስከ 100 ሺህ ብር ገቢ ታገኝ እንደነበረ አስታውሳለች።

አሁንም በተፈጠረው ሰላም የቀድሞ ስራዋን አጠናክራ ለመቀጠል መዘጋጀቷንም ገልጻለች።

በዓለም ቅርስነት በተመዘገበው አክሱምና አካባቢው ከ500 በላይ የተለያየ ቅርጽና ዲዛይን ያላቸው ከአንድ ወጥ ድንጋይ የተሰሩ ሀውልቶች አሉ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም