በቀጣይ አስር ቀናት የዝናቡ መጠንና ስርጭት ተጠናክሮ ስለሚቀጥል ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል -የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት - ኢዜአ አማርኛ
በቀጣይ አስር ቀናት የዝናቡ መጠንና ስርጭት ተጠናክሮ ስለሚቀጥል ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል -የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት
አዲስ አበባ ሰኔ 6/2015(ኢዜአ)፡- በቀጣይ አስር ቀናት የዝናብ መጠንና ስርጭት ተጠናክሮ ስለሚቀጥል ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳሰበ።
ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው የሚቲዎሮሎጂ ትንበያ በመጭዎቹ አስር ቀናት በምዕራብ፣ በደቡብ ምዕራብ፣ በሰሜን ምዕራብና መካከለኛው ኢትዮጵያ ለክረምት ዝናብ መፈጠር ምክንያቶች ተስተውለዋል።
በዚህም በወለጋ፣ በሸዋ፣ በጅማ፣ ኢሊባቦር፣ በሐረርጌ፣ አርሲና ባሌ ዞኖች፣ እንዲሁም በጎጃም፣ አዊ፣ ሰሜንና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች፣ የምዕራብ፣ ሰሜንና መካከለኛው ትግራይ ዞኖች፣ በሲዳማ፣ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ፣ ደቡብና እና ደቡብ ምዕራብ ክልል አብዛኛው ዞኖች የተቀራረብና ከባድ ዝናብ ያገኛሉ።
በትንበያው መሰረት የዝናብ ስርጭትና መጠኑ የተሻለ ስለሚሆን የአፈር እርጥበት ለግብርና እንቅስቃሴ ለማከናወን ለተዘሩ ሰብሎች ውሃ ፍላጎት ለማሟላትና የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና የመኖ ሳር ልምላሜ በጎ ተጽዕኖ እንደሚኖረው አስታውቋል።
ነገር ግን በተለይም በምዕራብ አጋማሽ ኢትዮጵያ አካባቢ የሚኖረው የዝናብ መጠንና ስርጭት ለአፈር መሸርሸር፣ መሬት መንሸራተትና ጎርፍ ሊያስከትል ስለሚችል ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ገልጿል።
ለአብነትም በአባይ፣ በተከዜ፣ የላይኛውና መካከለኛው ኦሞ፣ ጊቤ፣ አዋሽ፣ ስምጥ ሸለቆ፣ ገናሌና ዳዋ፣ ዋቢ ሸበሌ ተፋሰሶች የሚመለከተው አካል ብርቱ ክትትልና ትኩረት እንዲደረግ ትንበያው አመልክቷል።