ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በያገባኛል መንፈስ በትብብር ሊሰሩ ይገባል--ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ - ኢዜአ አማርኛ
ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በያገባኛል መንፈስ በትብብር ሊሰሩ ይገባል--ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ
ጋምቤላ ሰኔ 6/2015(ኢዜአ)፦ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በያገባኛል መንፈስ በትብብር መሥራት እንደሚገባቸው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ።
ኮሚሽኑ በጋምቤላ ክልል ለሚያካሂደው የአጀንዳ ማሰባሰብና የተሳታፊ አካላት ምልመላን ለሚያግዙ ተባባሪ አካላት ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ስልጠና መስጠት ጀምሯል።
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ስልጠናውን ባስጀመሩበት ወቅት እንዳሉት ባለድርሻ አካላት በያገባኛል መንፈስ ለዘላቂ ሰላም በመስራት ሁሉም እኩል ተጠቃሚ የሚሆንባትን የተሻለች ኢትዮጵያን መገንባት ይጠበቅበታል።
ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ልዩነቶችና ያለመግባባቶችን በውይይት በመፍታት ሁሉም ያለ ልዩነት እኩል ተጠቃሚ የሚሆንባት የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት በትብብር እንዲሰራ ጠይቀዋል።
ስልጠናው ኮሚሽኑ በቀጣይ ለሚያከናውናቸው የተሳታፊ ምልመላና የአጀንዳ መሰበሰብ ስራ የሚያግዙ ተባባሪ አካላትን አቅም ለመገንባት ያለመ መሆኑንም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ ባዘጋጀው ስልጠና ላይ የሲቪክ ማህበራት፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
ሰልጣኞቹ በሚኖራቸው የሁለት ቀናት ቆይታ በምክክር ጽንሰ ሃሳብ፣ በኮሚሽኑ ተግባርና ኃላፊነት፣ ተባባሪ አካላት በልየታ ወቅት በሚኖራቸው ሚና ዙሪያ ገለፃ እንደሚደረግላቸው ከመርሃ ግብሩ ለማወቅ ተችሏል።