ኢትዮጵያና ኢንዶኔዥያ በንግድና ኢንቨስትመንት መስክ ያላቸውን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በትብብር እየሰሩ ነው- አምባሳደር አል ቡሲራ ባስኑር - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ኢንዶኔዥያ በንግድና ኢንቨስትመንት መስክ ያላቸውን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በትብብር እየሰሩ ነው- አምባሳደር አል ቡሲራ ባስኑር
አዲስ አበባ ሰኔ 6/2015 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያና ኢንዶኔዥያ በንግድና ኢንቨስትመንት መስክ ያላቸውን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በትብብር እየሰሩ መሆኑን በኢትዮጵያ የኢንዶኔዥያ አምባሳደር አል ቡሲራ ባስኑር ገለጹ።
በኢትዮጵያ የኢንዶኔዥያ አምባሳደር አል ቡሲራ ባስኑር ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አገራቱ በሁሉም መስኮች ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳደጉ መጥተዋል፡፡
በተለይ በኢኮኖሚው መስክ ያሉ እድሎችን ከመጠቀም ባሻገር የሁለቱን አገራት ኢኮኖሚ የሚያጠናክሩ አዳዲስ እድሎች እየተፈጠሩ ስለመሆኑ ገልጸዋል።
በዚህም በርካታ የኢንዶኔዥያ ባለሃብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በተለይ በጨርቃጨርቅና ዘርፍ ላይ በስፋት እንደተሰማሩ ተናግረዋል፡፡
ሌሎች የኢንዶኔዥያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎታቸው እየጨመረ መምጣቱንም ነው ያነሱት፡፡
በዚህም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት በኢኮኖሚው መስክ ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አምባሳደሩ ገልጸዋል።
በፈረንጆቹ 2022 በኢንዶኔዥያ አዘጋጅነት በጃካርታ በተካሄደው የንግድ ባዛር ላይ 79 የኢትዮጵያ ባለሃብቶች የተሳተፉ ሲሆን፤ ይህም አገራቱን በኢኮኖሚው መስክ ይበልጥ በማስተሳሰር ረገድ ትልቅ ጅማሮ ነው ብለዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በርካታ የኢንዶኔዥያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ያሉ ምቹ ሁኔታዎችን ሲመለከቱ መቆየታቸውን ጠቅሰው፤ በዚህም በፋርማሲቲካል እና ምግብ ማቀነባበር ዘርፍ ለመሰማራት በሂደት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያና ኢንዶኔዥያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የመሰረቱት እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1961 ሲሆን ኢንዶኔዠያ ኤምባሲዋን በ1964 በአዲስ አበባ መክፈቷ ይታወሳል።