በሀገራዊ የምክክር መድረኩ ሂደት የመደማመጥ እሴት ጎልቶ ሊታይ ይገባል - የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች - ኢዜአ አማርኛ
በሀገራዊ የምክክር መድረኩ ሂደት የመደማመጥ እሴት ጎልቶ ሊታይ ይገባል - የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች
ሚዛን አማን ሰኔ 06/2015 (ኢዜአ) የሀገራዊ ምክክሩ ሂደት ስኬታማ እንዲሆን የመደማመጥ እሴትን ጠብቆ ለውይይት መቅረብ እንደሚገባ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ገለጹ።
የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች የሀገራዊ ምክክሩን ሂደት አስመልክተው ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት "የኔ ሀሳብ ብቻ" የሚል አመለካከትን በማስወገድ የጋራ መፍትሄ ለማምጣት ራስን ማዘጋጀት ያስፈልጋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የኮንታ ወረዳ ቤተ ክህነት አገልጋይ ቄስ ቤዛ ጥላሁን እንዳሉት በንግግር ጊዜ ትህትናን መላበስ መግባባትን ለመፍጠር ትልቅ ኃይል እንዳለው ገልጸዋል።
"በመላው ሀገራችን የሚደረገው የምክክር ሂደትም ውጤታማ እንዲሆን ኢትዮጵያዊያን የመደማመጥ እሴትን መሠረት ተደርጎ ማካሄድ ይገባናል"ብለዋል።
በተለይ ለውይይቱ ከየአካባቢው በተለያዩ አደረጃጀቶች ስር የሚወከሉ የውይይቱ ተሳታፊዎች የራሳቸውን ሐሳብ ከመግለጽ ባሻገር፤ የሌሎችን ሀሳብ በማዳመጥ ለጋራ ሰላም በተረጋጋ መንገድ መነጋገር ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
እንደ ሃይማኖት አስተምህሮ የሌላውን ክብር ከራስ ይልቅ ከፍ ማድረግ የትልቅነት ማሳያ መሆኑን አመልክተው፣እውነተኛ ሰላምና ሀገራዊ ዕድገት እንዲመጣ የሌላን ሰው ሀሳብ እንደ ሀሳብ ማክበር ይገባል በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
''እንደ ሀገር እየገጠሙን ያሉ ፈተናዎችን ለማለፍ ያለን ብቸኛ አማራጭ መነጋገር ነው'' ያሉት ቄስ ቤዛ፣ ተነጋግሮ ለመተማመን ጆሮና ልብን ክፍት አድርጎ ለውይይት መቅረብ ተገቢ መሆኑን አመልክተዋል።
ሰላም በሚያመጡ ሀሳቦች ላይ በአንድነት በመቆም በጋራ መስራት ያስፈልጋል ሲሉም አሳስበዋል።
በሸካ ዞን የየኪ ወረዳ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ፋሪስ ሙሳ በበኩላቸው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ከታችኛው መዋቅር ተነስቶ ሥራ መጀመሩ ውጤታማነቱ ላይ ተስፋ እንዳሳደረባቸው ገልጸዋል።
የመነጋገርና ችግሮችን በውይይት የመፍታት እሴት በምክክሩ ይጎለብታል የሚል እምነት እንዳላቸው በማመላከት።
በመሆኑም በውይይቱ ወቅት "የኔ ይበልጣል" ከሚል አስተሳሰብ በመውጣት የተሻለውንና የጋራ ሀገራዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ጉዳዮች ላይ ተደማምጦ መግባባት ላይ ማተኮር ያስፈልጋል ብለዋል።
ከምንም በላይ ሰላምና ኢትዮጵያዊ አንድነትን የማጽናት እሳቤን ይዞ መወያየት እንደሚያስፈልግም አጽንኦት ሰጥተዋል።
በኮንታ ዞን የጭዳ ከተማ አስተዳደር የሀገር ሽማግሌ አቶ ታፈሰ ምተታ እንዳሉትም "ምክክሩ የሰላማችን ዋስትና ይሆናል ብለን ተቀብለን ከኮሚሽኑ ጋር እየሰራን ነው" ብለዋል።
በምክክር ሂደቱ ''ተጎዳን'' የሚሉ አካላት ጉዳት ተሰምቶ በሀገራዊ መፍትሄ የሚታከም መሆኑን ገልጸው፣ የውይይቱ ተሳታፊዎች በሀገራዊ ሃላፊነት ስሜት ሀሳባቸውን ማንሸራሸር እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።
"ጉዳዮቻችን ላይ ተነጋግረን መስማማት ከቻልን የሚገጥሙንን ሀገራዊ ፈተናዎች እንሻገራለን" ያሉት አቶ ታፈሰ፣ በአካባቢያቸውም ተሳታፊዎችን በመመልመልና መሰል ተግባራት ላይ በመሳተፍ ሂደቱን እየደገፉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከተባባሪ አካላት ጋር በመወያየት የአጀንዳ አሰባሰብና የተሳታፊ ምርጫ ሂደት እያካሄደ ነው።