ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ጨምሮ የአራት አገራት መሪዎች የሱዳንን ችግር ለመፍታት ከጀነራል አብዱል ፋታህ አል-ቡርሃንና ከጀነራል መሐመድ ሀምዳን ዳጋሎ ጋር ውይይት ያደርጋሉ -ኢጋድ

አዲስ አበባ ሰኔ 6/2015(ኢዜአ):-የሱዳን ወቅታዊ ሁኔታን ለመፍታት የኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያና ደቡብ ሱዳንን ያካተተው የአራትዮሽ ስብስብ ከጀነራል አብዱል ፋታህ አል-ቡርሃንና ከጀነራል መሐመድ ሀምዳን ዳጋሎ በቀጣይ 10 ቀናት ውስጥ በአካል ለመወያየት መወሰኑን የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) አስታወቀ።

14ኛው የኢጋድ የመሪዎች ጉባኤ ትናንት በጅቡቲ መካሄዱ ይታወቃል።

በጉባኤው የኢጋድ አባል አገራት መሪዎች እና ባለስልጣናት የተሳተፉ ሲሆን ቀጣናዊ ተቋሙ በምስራቅ አፍሪካ እየተከናወኑ ላሉ ስራዎች እየሰጠ ያለውን ምላሽ ጨምሮ በተለያዩ ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።


 

ጉባኤው ከመከረባቸው ጉዳዮች አንዱ የሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ ሲሆን የተለያዩ የውሳኔ ሀሳቦችን አሳልፏል።

የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ጉባኤው የኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ፣ ኬንያ እና ደቡብ ሱዳን መሪዎች ስብስብ (ኳርቴት) ከጀነራል አብዱል ፋታህ አል-ቡርሃን እና ከጀነራል መሐመድ ሀምዳን ዳጋሎ ጋር በቀጣይ 10 ቀናት በመገናኘት ውይይት እንዲያደርግ መወሰኑን ገልጸዋል።

አገራቱ ኢጋድን ወክለው እንደሚወያዩ እና ውይይቱ በሱዳን ተባብሶ የቀጠለውን ጦርነት ማስቆም፣ ሁሉም አይነት ግጭቶች እንዲቆሙ እና ሁለቱ ወታደራዊ አመራሮች ጦርነቱን ለማቆም ቁርጠኛ አቋም እንዲወስዱ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ መሆኑን አመልክተዋል።

በዚህም የዜጎችን ሕይወት ለመታደግ እንዲሁም እየወደመ ያለውን ንብረትና ሌሎች አይነት ውድመቶችን ማስቆም እንደሚቻልም ተናግረዋል።

በተያያዘም በቀጣይ ሁለት ሳምንታት ከጀነራል አብዱል ፋታህ አል-ቡርሃን እና ከጀነራል መሐመድ ሀምዳን ዳጋሎ ጋር የሰብአዊ እርዳታ ኮሪዶር መክፈት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት ለማድረግ ከስምምነት ላይ መደረሱን ነው የኬንያው ፕሬዝዳንት የጠቆሙት።

የኮሪዶሩ መከፈት አስቸኳይ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው በተለይም ሴቶች፣ሕጻናት፣ በግጭቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች እና ሌሎች ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ ዜጎች የሰብአዊ ድጋፍ ለማቅረብ እንደሚያስችል ገልጸዋል።

በተጨማሪም በቀጣይ ሶስት ሳምንታት በሱዳን ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ምክክር ሂደት ለመጀመር የመሪዎች ጉባኤው ከስምምነት ላይ መድረሱን ነው ዊሊያም ሩቶ የተናገሩት።

የምክክሩ አላማ የሱዳን ሕዝብ የሚወያይበት እና መፍትሔ የሚያበጅበት እድል መፍጠር እንደሆነ አመልክተዋል።

ከዚህ ቀደም ኢጋድ በሱዳን ያለውን አለመረጋጋት ለመፍታት ሶማሊያ፣ኬንያ እና ደቡብ ሱዳን ያሉበት የሶስትዮሽ ስብስብ መመስረቱን ያስታወሱት ሩቶ በአሁኑ ስብስብ ውስጥ ኢትዮጵያ መካተቷን ጠቁመዋል።

ኬንያ በሊቀ-መንበርነት የምትመራው የአራትዮሽ ስብስብ(ኳርቴት) በሱዳን ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም