ዓለም አቀፍ የደም ለጋሾች ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ በአሶሳ ከተማ ይከበራል-ጤና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ዓለም አቀፍ የደም ለጋሾች ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ በአሶሳ ከተማ ይከበራል-ጤና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ሰኔ 6/2015 (ኢዜአ):-ዓለም አቀፍ የደም ለጋሾች ቀን በኢትዮጵያ ለ20ኛ ጊዜ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ እንደሚከበር የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
ቀኑ “ደም እንለግስ፤ ሕይወት እናጋራ፤ ዘወትር እናጋራ" በሚል መሪ ሀሳብ ነገ እንደሚከበር ተገልጿል።
በአሶሳ ከተማ የሚከበረውን የዓለም ደም ለጋሾች ቀን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ደምና ህብረ-ህዋስ ባንክ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ታዬ ቀኑ ደም መለገስን በተመለከተ የግንዛቤ ስራ በመስራት፣ ለደም ለጋሾች ማበረታቻና እውቅና በመስጠት እንዲሁም ምስጋና በማቅረብ እንደሚከበር ገልጸዋል።
በ2015 በጀት ዓመት እስከ አሁን 320 ሺህ ዩኒት ደም በማሰባሰብ እና አስፈላጊውን ምርመራ አድርጎ በማሰራጨት ዜጎች በደም ዕጦት ምክንያት ሕይወታቸውን እንዳያጡ መታደግ መቻሉን አመልክተዋል።
ይሁንና ከሚፈለገው አንጻር ለሁሉም ለማዳረስ እየተከናወነ ያለው ስራ መቀጠል አለበት ነው ያሉት አቶ ሀብታሙ።
ደም ለጋሾች እያደረጉ ላሉት ሰብዓዊ አገልግሎት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ደምና ህብረ-ህዋስ ባንክ አገልግሎት የጥራት እና ሜዲካል ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ጤናዬ ደምሴ በበኩላቸው በየዓመቱ የሚለገሰው ደም መጠን እየጨመረ ቢሆንም ከሚፈለገው አቅርቦት አንጻር ቀሪ ስራዎች እንዳሉ ገልጸዋል።
ቋሚ ደም ለጋሾችን በማፍራት የበርካቶችን ሕይወት መታደግ እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል።
ዓለም አቀፍ የደም ለጋሾች ቀን ከአሶሳ በተጨማሪ በመላው ኢትዮጵያ በሚገኙ ደም ባንኮች እንዲሁም በአዲስ አበባ በተከታታይ መርሐ-ግብሮች እንደሚከበር የጤና ሚኒስቴር በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መረጃ አስታውቋል።