የአፍሪካ-እስያ ወጣቶችን የኢኮኖሚና ማህበራዊ ትስስርና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በጋራ መስራት ይገባል-ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ-እስያ ወጣቶችን የኢኮኖሚና ማህበራዊ ትስስርና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በጋራ መስራት ይገባል-ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ
አዲስ አበባ ሰኔ 5/2015(ኢዜአ)፡- የአፍሪካ-እስያ ወጣቶችን የኢኮኖሚና ማህበራዊ ትስስርና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ቀጣይነት ባለው መንገድ በጋራ መስራት እንደሚገባ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገለጹ።
በ''ኦየስ-ግሎባል ፋውንዴሽን'' አዘጋጅነት ከአፍሪካና እስያ አህጉር የተውጣጡ ወጣቶች መድረክ ዛሬ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
በመርሐ-ግብሩ መክፈቻ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፣ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ፣ የአፍሪካና እስያ ሀገራት ዲፕሎማቶችና ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የመድረኩ ዋና አላማ የአፍሪካና የእስያ ወጣቶች በስራ ፈጠራ፣ በጤና፣ በአካባቢያዊ የአየር ንብረት ለውጥ፣ በሰላም፣ በበጎ ፈቃደኝነት እና በሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች እውቀትና ልምድ እንዲጋሩ በማድረግ ወጣቶችን ለማብቃት ታሳቢ ያደረገ መሆኑ ተገልጿል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ ወጣቶች በሀገራት የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና ማህበራዊ ተሳትፎ ላይ ቁልፍ ሚና ያላቸው መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም ወጣቶች በአመራር፣ በስራ ፈጠራ፣ በኢኮኖሚና ሰላም በማስፈን ሁሉን አቀፍ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ቀጣይነት ያለው ስራ በጋራ መስራት ይገባል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የኢንዶኔዥያ አምባሳደር አል ቡሲራ ባስኑር በበኩላቸው፣ ወጣቶች የሀገራቱ ሁሉ የኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ለውጦች ዋነኛ ተዋናይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
አፍሪካንና እስያን በወጣቱ ኃይል ተሳትፎ ማስተሳሰር ለሁለቱ አህጉሮች እና ለዓለም በጎ አስተዋጽኦ ስለሚኖረው አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ በበኩላቸው፤ አፍሪካና እስያ በወጣቶች ቁጥር ከዓለም ሰፊውን ድርሻ መያዛቸውን በማንሳት ይህም ለዘላቂ ልማት ትልቅ አቅም ነው ብለዋል።
ዘላቂ ልማት ያለ ዘላቂ ሰላም የማይታሰብ በመሆኑ ወጣቶች ሰላምን በአስተማማኝነት ለማስፈን ያላቸውን ሚና እንዲወጡ መስራት ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።
የኦ-የስ ግሎባል ፋውንዴሽን መስራችና ባለቤት አቶ ከማል አብደላ፤ የመድረኩ ዓላማ ወጣቶች፣ በስራ ፈጠራ፣ በሰላምና በጎ አድራጎት እና ሌሎችም ዘርፎች ያላቸውን አቅም በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲያውሉ ለማድረግ ነው ብለዋል።
በመድረኩ የተሳተፉ ወጣቶች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ መድረኩ በየዘርፉ ያሉ በርካታ ልምዶችን እንዲለዋወጡ ትልቅ እድል እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።
የአፍሪካ-እስያ የወጣቶች የትስስር መድረክ በነገው ዕለት በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።