በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ተግባራዊ የሚደረግ የ20 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የመልሶ ማቋቋምና ግንባታ ፕሮግራም ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ተግባራዊ የሚደረግ የ20 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የመልሶ ማቋቋምና ግንባታ ፕሮግራም ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ ሰኔ 5/2015 (ኢዜአ) ፦ በኢትዮጵያ ግጭት ተከስቶባቸው በነበሩ አካባቢዎች ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ተግባራዊ የሚደረግ የ20 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የመልሶ ማቋቋምና ግንባታ ፕሮግራም ይፋ ሆነ፡፡
የኢትዮጵያ መልሶ ማቋቋም እና መገንባት የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሺዴ፤ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በተከሰተ ግጭት ምክንያት የደረሰውን የጉዳት መጠን በመለየት የመልሶ ግንባታ ስራ ለማካሄድ ጥናት ሲካሄድ መቆየቱን ገልጸዋል።
ጥናቱም በጦርነት ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ባስተናገዱት የአማራ፣ ትግራይ፣ አፋርን ጨምሮ በተወሰኑ የኦሮሚያና ቤንሻንጉልና ደቡብ ክልሎች መካሄዱን አንስተዋል።
የመልሶ ግንባታና ማቋቋም ስራ የሚመራበትን እቅድና አደረጃጀት ልየታ በማድረግ አመላካች የጥናት ውጤት የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ለልማት አጋሮች ይፋ መደረጉንም አስረድተዋል።
በቀጣይ በጦርነት ምክንያት የወደሙ መሰረተ ልማቶችን በመገንባት የዜጎችን ህይወት ለማሻሻል ከሚከናወኑ ስራዎች ባሻገር ሰላምና ማጽናትና አገራዊ አንድነትን ለማጠናከር በትብብር መስራት ይገባል ነው ያሉት፡፡
ጥናቱን መነሻ በማድረግ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ለመልሶ ግንባታና ማቋቋም የልማት ስራ 20 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል።
መንግስት ለመልሶ ግንባታና ማቋቋም የልማት ስራ በጀት መድቦ ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰው፤ በቀጣይም የልማት አጋሮች ድጋፍ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል ብለዋል።
የመልሶ ግንባታና ማቋቋም ስራው በግጭቱ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ያስተናገዱትን የአማራ፣ ትግራይ፣ አፋርን ጨምሮ በተወሰኑ የኦሮሚያ፣ ቤንሻንጉልና ደቡብ ክልሎች ተግባራዊ እንደሚደረግ አንስተዋል።
በሁለተኛው አገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያም የማክሮ ኢኮኖሚውን በማረጋጋት፣ የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ፣ የውጭ ምንዛሬ እና የግሉን ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ ለማሳደግ በትኩረት የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ፣ የጥናት ግኝቱ በተለያዩ አገሪቷ ክፍሎች በተፈጠሩ ግጭቶች የደረሰውን ውድመት መልሶ ለመገንባትና ለማቋቋም እንደሚረዳ ገልጸዋል።
በግጭቶች ተሳታፊ የነበሩ የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ መደበኛ ህይወት ለመመለስ ከክልል መስተዳደር እና ከልማት አጋሮች ጋር በትብብር እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የመልሶ ማቋቋምና ግንባታ ስራውም የአማራ፣ የትግራይ፣ የአፋርን ጨምሮ በተወሰኑ የኦሮሚያ፣ ቤንሻንጉልና ደቡብ ክልሎች በግጭት ተሳታፊ የነበሩ ታጣቂዎችን እንደሚያካትት ገልጸዋል።
የመልሶ ማቋቋም ስራን በስኬት ተግባራዊ ለማድረግ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት የተደራጀ ስራ ያስፈልጋል ያሉት ደግሞ የመድረኩ ተሳታፊ እና በዓለም አቀፉ የእድገት ማዕከል ኢኮኖሚስት የሆኑት ቴዎድሮስ መኮንን ናቸው።
ለዚህም መንግስት የመልሶ ግንባታና ማቋቋም ስራዎችን በተደራጀ መልኩ ለማቅረብ የሚያከናውናቸው ስራዎች የዋጋ ግሽበት እንዳያስከትሉ ጥንቃቄ ማድረግ ይፈልጋል ብለዋል።
በጥናቱ መነሻነትም በመልሶ ግንባታ ስራው ላይ የልማት አጋሮችን ተሳትፎ በማሳደግ የሚገኘውን ሃብት በተቀናጀ መንገድ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባም ተናግረዋል።
ጥናቱ በተካሄደባቸው ክልሎች በግጭት ምክንያት በማህበራዊ፣ በምርት፣ በመሰረተ ልማት እና ባለብዙ ዘርፎች አጠቃላይ 22 ነጥብ 69 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ውድመት መድረሱ ተጠቁሟል።
በመድረኩም የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ፣ ሚኒስትሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ የልማት አጋሮችና የተቋማት የስራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡