ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የፍትህ ስርዓቱን ቀልጣፋ፣ዘመናዊና ተደራሽ ለማድረግ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ-ፍትህ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ሰኔ 05/2015 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ የፍትህ ስርዓቱን ቀልጣፋ፣ዘመናዊና ተደራሽ ለማድረግ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የፍትህ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት(USAID)''የፍትህ ስርዓት ግንባታ በኢትዮጵያ'' በሚል ለአራት ዓመታት ሲያከናውን የቆየውን ፕሮጀክት የማጠቃለያ መርሃ ግብር ተካሂዷል፡፡


 

ፕሮጀክቱ በዋናነት የፍትህ ስርዓቱን ማሻሻል ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡

በፍትህ ሚኒስቴር የፍትህ ስርዓት ማሻሻያና የለውጥ አመራር ዳይሬክተር ኖህ ታከለ እንደገለጹት መንግስት የፍትህ ስርዓቱን ለማሻሻል የተለያዩ የለውጥ ስራዎችን አከናውኗል።

በተለይም የፍትህ ጥያቄ በብዛት የሚነሳባቸው ተቋማትና ዘርፎችን በመለየት የማሻሻያ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በማሻሻያ ተግባራት ላይ የአጋር አካላት የበኩላቸውን ተሳትፎ ማድረጋቸውን ጠቅሰው፤ ላለፉት አራት ዓመታት በፍትህና በዲሞክራሲ ተቋማትና  በተመረጡ ክልሎች ሲተገበር የነበረው ፕሮጀክት የዚሁ አካል መሆኑን ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ ያስገኛቸውን ጠቀሜታዎች ከግምት በማስገባት መሰል የለውጥ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ጠቁመዋል፡፡

የመርሃ-ግብሩ ተሳታፊ የሆኑት የፍትህና የዲሞክራሲ ተቋማት በበኩላቸው ፕሮጀክቱ የፍትህ ስርዓቱን ለማሻሻል በሚደረገው ጥራት ላይ አዎንታዊ ሚና መጫወቱን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ እና ኢትዮጵያ እምባ ጠባቂ ተቋም ዋና እምባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ኃይሌ፤ ፕሮጀክቱ የተቋማቸውን አሰራር ለማዘመን ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡


 

ይህም ቀልጣፋ አሰራር ገቢራዊ እንዲያደርጉ ማገዙን ነው የገለጹት፡፡


 

የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ጌዛሊ አባሲማል እና የአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ ገረመው ገብረጻዲቅ በበኩላቸው፤ የፍትህ ስርዓትን ተደራሽ ከማድረግ አኳያ የዲጂታል አሰራሮችን ማስረፅና ሙያተኞችን ማብቃት ላይ አበረታች ስራዎች መከናወናቸውን ይገልጻሉ።

በተጨማሪም የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግርን በማድረግም እንዲሁ ተሞክሮዎችን ማስፋት ሌላኛው በፕሮጀክቱ የተገኙ ውጤቶች  መሆናቸውን ተናግረዋል።

በአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት(USAID)የፍትህ ተግባራት በኢትዮጰያ ፕሮጀክት ምክትል ኃላፊ  ማንደፍሮት በላይ፤ ፕሮጀክቱ በእውቀት ሽግግር፣ በአቅም ግንባታና በግብዓት አቅርቦት ላይ ትኩረት አድርጎ ሲከናወን መቆየቱን ተናግረዋል።

በዋናነት የዲሞክራሲና የፍትህ ተቋማት በፕሮጀክቱ የተካተቱ ሲሆን፤ በተመረጡ ክልሎች ፕሮጀክቱ ተግባራዊ እንዲሆኑ ተደርጓል።

በዚህም በመጀመሪያው ዙር አማራና ኦሮሚያ ክልሎች በፍትህ ስርዓት ማሻሻያ ድጋፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን ገልጸው፤  በቀጣይ ሌሎች ክልሎችን የማሳተፍ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም