በኤሌክትሪክ ኃይል መሰረተ ልማት ላይ የሚፈፀም ስርቆትን መከላከል የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል-የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል - ኢዜአ አማርኛ
በኤሌክትሪክ ኃይል መሰረተ ልማት ላይ የሚፈፀም ስርቆትን መከላከል የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል-የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል
አዲስ አበባ ሰኔ 5/2015 (ኢዜአ)፦ በኤሌክትሪክ ኃይል መሰረተ ልማት ላይ የሚፈፀም ስርቆትን በመከላከል በሀገር ላይ የሚደርስ ኪሳራን መቀነስ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ሊሆን እንደሚገባው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ገለጸ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ ምሰሶዎች ላይ የሚፈጸመውን ስርቆት ለመከላከል የብረት ማቅለጫ ድርጅቶች የሚኖራቸውን ሚና በተመለከተ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በማዕከላዊ ሁለት ሪጅን የትራንስሚሽን እና ሰብስቴሽን ኦፕሬሽን መምሪያ ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ዘበርጋ፤ በምስራቅ ሸዋ ዞን ለሚገኙ ኢንዱስትሪዎች በቂ ኃይል ማቅረብ የሚያስችሉ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች ላይ ዝርፈያ እየተፈጸመ መሆኑን ገልጸዋል።
በዞኑ አደአ ወረዳ ከለላና ጎበስዬ ቀበሌዎች እንዲሁም ቢሾፍቱ ከተማ፣ በድሬ ወረዳ ቃጅማ ቀበሌ፣ ዱከም ከተማ ኮትቻ ቀበሌ ከፍተኛ የመሰረተ ልማት ስርቆት የሚታይባቸው ናቸው ብለዋል።
በዚህ በጀት ዓመት 25 የኤሌክትሪክ ሃይል ማስተላለፊያ የብረት ምሰሶዎች ላይ 1 ሺህ 405 ብረቶች መሰረቃቸውን በመጥቀስ፤ የብረት ማቅለጫ ፋብሪካዎች ችግሩን ለመከላከል እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
ለዚህም ከኤሌክትሪክ ምሰሶዎች የተሰረቁ ብረቶች ለፋብሪካዎቹ በሽያጭ ሲቀርቡ በማጋለጥ ወንጀለኞችን ተጠያቂ ለማድረግ የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው ገልዋል።
በውይይቱ የተሳተፉ የከፍተኛ ሃይል ተጠቃሚ ኢንዱስትሪ ተወካዮች በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ በሚፈጸም ስርቆት የኃይል መቆራረጥ በመኖሩ የፋብሪካዎች የማምረት አቅም ላይ እንቅፋት መፍጠሩን አንስተዋል።
በመሆኑም በኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ላይ የሚፈጸመውን ስርቆት ለመግታት የሁላችንም የነቃ ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው ብለዋል።
ከፍተኛ የኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች በሚገኙባቸው አካባቢ ያለው ህብረተሰብ መሰረተ ልማቶችን በባለቤትነት እንዲጠብቅ የግንዛቤ ስራዎችን ማስፋት ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።
መንግስት በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ ስርቆት የሚፈጽሙ አካላት ብረት ይዘው ወደ ፋብሪካዎቹ ሲመጡ የብረቱን ዓይነት ከመለየት ጀምሮ ወንጀለኞችን እንደሚያጋልጡና አስተማሪ እርምጃ እንዲወሰድ እንደሚሰሩ ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኃይል የትራንስሚሽን ኦፕሬሽን ዘርፍ ስራ አስፈጻሚ አቶ ሀብታሙ ውቤ በበኩላቸው ከፍተኛ የኃይል ተጠቃሚ የሆኑ ኢንዱስትሪዎች የሚያጋጥማቸውን የኃይል መቆራረጥ ለመቅረፍ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
ለዚህም ሰብስቴሽኖችን እንዲሁም የከፍተኛ ኤሌክትሪክ ኃይል የማስተናገድ አቅም ያላቸው የማሰራጫ መስመሮችን በተለያዩ አካባቢዎች መገንባቱን ተናግረዋል።
ሆኖም የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ በአንዳንድ አካላት በሚፈፀም ስርቆት ሳቢያ የኃይል መቆራረጥ፣ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ እና ለመልሶ ግንባታ የውጭ ምንዛሬን ጨምሮ በርካታ ጉዳቶችን ማስከተሉን ጠቅሰዋል።
በ2014 በጀት ዓመት በኤሌከትሪክ መሰረተ ልማት ላይ በደረሰ ስርቆትና ውድመት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል 104 ሚሊዮን ብር ኪሳራ ማስተናገዱን ገልጸው፤ የ2015 በጀት ዓመት የጉዳት መጠንም እየተጠና ነው ብለዋል።
በሃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ የሚደርሰው ጉዳት በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳርፈው አሉታዊ ጫና ከፍተኛ በመሆኑ በወንጀለኞች ላይ ጠንካራ እርምጃ እንዲወሰድ ሁሉም ሃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን ደህንነት ለማስጠበቅ ሁሉም ዜጋ ሀገራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።