ቀጥታ፡

የሀገሪቱን የቡና ምርታማነትን ለማሻሻል የሚያግዝ ፕሮጀክት ተቀርጾ ወደ ስራ ተገብቷል -የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት 

አዲስ አበባ ሰኔ 5/2015 (ኢዜአ)፡- የሀገሪቱን የቡና ምርታማነትን ለማሻሻል የሚረዳ ፕሮጀክት ተቀርጾ ወደ ስራ መገባቱን የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ሀገር ከመሆኗ በተጨማሪ ጣዕም ያለው የተፈጥሮ ቡና ለዓለም ገበያ በማቅረብ ትታወቃለች።

ነገር ግን ኢትዮጵያ አሁንም ከዘርፉ በሚገባት ልክ ተጠቃሚ አለመሆኗ እሙን ነው፡፡

ይህንኑ በተመለከተ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት እና በጅማ የእርሻ ምርምር ማዕከል የሚከናወኑ የቡና ማሻሻያ ስራዎችን የተመለከተ መድረክ አዘጋጅቷል፡፡

በመድረኩም በዘርፉ የሚሰሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ በዚሁ ወቅት መድረኩ በኢትዮጵያ የቡናና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያግዙ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ለመውሰድ ይረዳል ብለዋል፡፡

በዚህም ችግሮችን ለመለየት እንዲሁም የተሻለ ምርትንና ጥራትን ለማግኘት የሚረዱ ሃሳቦችንና ተሞክሮዎችን ለመቅሰም እንችላለን ብለዋል።

በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የሰብል ምርምር ዳሬክተር ዶክተር ታየ ታደሰ በበኩላቸው ባለፉት ሁለት ዓመታት በስፋት የተከሰተው የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተለው ድርቅ ዘርፉን እንደጎዳው ጠቅሰዋል፡፡

የቡና ዝርያን ለማሻሻል መንግስት የተለያዩ ጥረቶች እያደረገ ቢሆንም አሁንም ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይም የቡና ምርታማነትን ለማሻሻል የሚያግዝ የ8 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ፕሮጀክት መቀረጹን ጠቅሰው ፤ፕሮጀክቱ በዋናነት ምርታማነትን የሚጨምሩ የቡና ዝርያዎችን ማሻሻል ላይ እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡

ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ለማድረግ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን ከመንግስት ጋር በማጣመር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በፕሮጀክቱ በመታገዝ በቀጣይ የተሻለ የቡና ምርት በማግኘት ገቢን ማሳደግ እንደሚቻልም ገልጸዋል።

ኢንስቲትዩቱ ከዓለም አቀፉ የቡና ምርምር ማዕከል ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ያለውን የቡና ምርት እምቅ አቅም፣ የመሰረተ ልማት ተደራሽነት እና በአገሪቱ እየተከናወነ የሚገኘውን የቡና ማሻሻያ በተመለከተ ጥናት ማከናወኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ቀድመው የተሰሩ ፕሮጀክቶችንና በጥናት ውጤቱ የተገኙ ልምዶችን በመቀመር በመጪዎቹ ስድስት ዓመታት የሚተገበር ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡

 

 

 

 

   

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም