የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የተቋማትን የተግባቦት ስርዓት በማሻሻል ረገድ የበኩሉን ሚና እየተወጣ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የተቋማትን የተግባቦት ስርዓት በማሻሻል ረገድ የበኩሉን ሚና እየተወጣ ነው
አዲስ አበባ ሰኔ 5/2015 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) የተቋማትን የተግባቦት ስርዓት በማሻሻል ረገድ የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን ገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ለገቢዎች ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ለሁለት ሳምንት ሲሰጥ የቆየውን ሥልጠና አጠናቋል፡፡
ስልጠናው በመልዕክት ቀረፃ ፣በንግግር ፅሑፍ አዘገጃጀትና በይዘት ቀረጻ ላይ ያተኮረ ነው።
የኢዜአ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ተፈራ በቀለ በዚሁ ወቅት፤ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት መረጃን ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎችን በስልጠና ለማብቃት የበኩሉን ሚና እየተወጣ ይገኛል ብለዋል፡፡
የገቢዎች ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች የተሰጠው ስልጠና የዚሁ ስራ አካል መሆኑን ጠቅሰው፤ ባለሙያዎቹ በስልጠናው ያገኙትን እውቀትና ክህሎት ወደ ተግባር በመቀየር ውጤታማ ስራ እንደሚያከናውኑ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ኢዜአ በቀጣይም ከተለያዩ ተቋማት ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለጽ፡፡
በኢዜአ የስልጠና ምክር እና ምርምር ማዕከል ሃላፊ አቶ አብዱራህማን ናስር በበኩላቸው ፤ኢዜአ ለተለያዩ የፌደራል እና የክልል ተቋማት በሚዲያና ኮሚኒኬሽን የአቅም ግንባታ ስልጠና እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ተቋሙ ስልጠና ከመስጠት ባሻገር ከተለያዩ ተቋማት ጋር ጠንካራ ግንኙነት በመፍጠር መረጃን ለህዝብ ተደራሽ እንዲሆን እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የገቢዎች ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አዲሱ ይርጋ ሚኒስቴሩ ሰፊ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን አደረጃጀት እንዳለው ጠቅሰው፤ የባለሙያዎችን አቅም በየጊዜው በስልጠና እያጠናከሩ መሄድ ያስፈልጋል ብለዋል።
የአገርን ገቢ በሚፈለገው ልክ ለመሰብሰብ በሚደረገው ርብርብ ውስጥ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላቸውም ነው የገለጹት።
በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በንድፈ ሀሳብና በተግባር በተደገፈ መንገድ የባለሙያዎቹን አቅም ለመገንባት የሰጠው ስልጠና ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል።
በገቢዎች ሚኒስቴር የህትመት እና ዶክሜንቴሽን ቡድን አስተባባሪ እስክንድር መርሃጽድቅ ስልጠናው ተግባር ተኮር እንደነበር ገልጸው፤ ክፍተቶቻቸውን ለመሙላት እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል፡፡
በሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ቡድን አስተባባሪ ሰለሞን ዘሪሁን በበኩላቸው ስልጠናው ለቀጣይ ስራቸው መቀላጠፍ አቅም የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከስልጠናው ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት ወደ ተግባር በመለወጥ ቁርጠኛ መሆናቸውንም ነው ያረጋገጡት፡፡