ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሕብረት ሥራ ኮሚሽን በቀናት ውስጥ የድርጊት መርሃ-ግብር አዘጋጅቶ እንዲያቀርብ የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ

አዲስ አበባ ሰኔ 5/2015(ኢዜአ):- ለሰባት ዓመታት የሥራ ማስፈጸሚያ ደንብና መመሪያ ሳይኖረው እየሰራ ያለው የኢትዮጵያ ሕብረት ሥራ ኮሚሽን እስከ ሰኔ 15 ቀን 2015 ዓ.ም የድርጊት መርሃ-ግብር አዘጋጅቶ እንዲያቀርብ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ፣ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

የመንግሥት ወጪ፣ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ሕብረት ሥራ ኮሚሽንን የ2013/14 የክዋኔ ኦዲት ገምግሟል።

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ፤ ኮሚሽኑ በአዋጅ ከተቋቋመ ሰባት ዓመት ቢሆነውም እስካሁን  የሥራዎቹ ማስፈጸሚያ ደንብና መመሪያ ሳያዘጋጅ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ ወጥ የሆነ የሒሳብ አያያዝ፣ የምርት ጥራት ደረጃና የኦዲትና የፋይናንስ መመሪያ ሥርዓት እንደሌለው ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤቱ ማረጋገጡንም ተናግረዋል።

የሕብረት ሥራ ማኅበራት ሀገራዊ ፋይዳና የገበያ ድርሻ በጥናት አለመለየቱን ገልጸው፤ እስካሁን ሦስት ጊዜያት የክዋኔ ኦዲት ተደርጎ ግብረ-መልስ ቢሰጠውም በግብረ-መልሱ መሠረት የዕቅዱ አካል አድርጎ የእርምት እርምጃ አልወሰደም ሲሉ ወቅሰዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ፣ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሮ አራሬ ሞሲሳ፤ ኮሚሽኑ ከተሰጠው ሥልጣንና ተልዕኮ አንፃር በአግባቡ እየተወጣ አለመሆኑን ጠቁመዋል።

ሕብረት ሥራ ኮሚሽን ተቋማዊ ግንባታ የሚመራው በደንብና መመሪያ ሳይሆን በግለሰቦች ፍላጎት ብቻ እንደሆነ ገልጸው፤ አሠራሩም የክትትልና ቁጥጥር ሥርዓት ያልዘረጋና ልዩ ድጋፍ የሚሹ ክልሎችን ያላማከለ እንደሆነ ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ ለሰባት ዓመታት የሥራ ማስፈጸሚያ ደንብና መመሪያ ሳይኖረው እስካሁን እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የፊታችን ሰኔ 15 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ የድርጊት መርሃ-ግብር አዘጋጅቶ ለቋሚ ኮሚቴው እንዲልክ አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ሕብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ጌታቸው መለሰ፤ በኮሚሽኑ ላይ የቀረቡ ሃሳቦች አግባብነት እንዳላቸው ጠቅሰው፤ በተሰጡ ግብረ-መልሶች መሠረት የማስተካከያ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን ገልጸዋል።

በቋሚ ኮሚቴው የተሰጡ አስተያየቶችን በሙሉ በቀጣይ ለማስተካከል በቁርጠኝነት እንሰራለን ሲሉም አረጋግጠዋል።

 


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም