አለመግባባቶችን በምክክር በመፍታት የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል--ሃገራዊ የምክክር ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
አለመግባባቶችን በምክክር በመፍታት የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል--ሃገራዊ የምክክር ኮሚሽን
ጋምቤላ ሰኔ 5/2015ነ(ኢዜአ)፦አለመግባባቶችን በምክክር በመፍታት የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩሉን ሚና እንዲወጣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ።
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ በጋምቤላ ክልል ከነገ ጀምሮ የሚካሄደውን የተሳታፊዎች ልየታና አጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት በማስመልከት በጋምቤላ ከተማ መግለጫ ሰጥተዋል።
ፕሮፌሰር መስፍን በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ኮሚሽኑ አለመግባባቶችን በምክክር በመፍታት የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት የተሰጠውን ተልዕኮ ለማሳካት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ በአዋጅ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ የአሰራር ስርዓቶችን በማዘጋጀት፤ጥናትና ምርምሮችን በማከናወንና ተቋማዊ አቅሙን በመገንባት ረገድ ሰፊ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሰዋል።
በአሁኑ ወቅትም ኮሚሽኑ የአጀንዳ ሀሳቦችን ከህዝቡ ለማሰባሰብ በያዘው እቅድ መሰረት ከነገ ጀምሮ በጋምቤላ ክልል ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የምክክር ሂደት ተሳታፊዎችን የመለየት ስራ ይጀምራል ብለዋል።
በክልሉ በዚሁ በሚጀመረው የልየታና አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት በወረዳ ደረጃ አብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል የሚወክሉ ዘጠኝ የማህበረሰብ አደረጃጀቶች መለየታቸውን ገልጸዋል።
ከተለዩት አደረጃጀቶች መካከል አርሶና ከፊል አርብቶ አደሮች ፣ ሴቶች፣ ወጣቶች ፣እድሮች፣ አባቶች፣ እናቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም እንደሚገኙበት አስገንዝበዋል።
ኮሚሽኑ የነዚህን የተሳታፊ ልየታ ተግባራት ለማከናወን በተባባሪነት ለሚሰሩ አካላት በቂ ስልጠና በመስጠት ወደ ስራ እንደሚገባም ተናግረዋል።
በተሳታፊ ልየታው በክልሉ የሚገኙ የሲቪክ ማህበራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤና ሌሎችም ተሳታፊ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል።
በመጨረሻም ኮሚሽኑ ለጀመራቸው ስራዎች መቃናት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍና ትብብር እንዲጠናከር ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል።