ሀገራዊ ምክክሩ ግጭቶችን በዘላቂነት በመፍታት በዜጎች መካከል የተሻለ ማህበራዊ ውል እንዲፈጠር ያደርጋል - አምባሳደር መሃሙድ ዲሪር - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ ግጭቶችን በዘላቂነት በመፍታት በዜጎች መካከል የተሻለ ማህበራዊ ውል እንዲፈጠር ያደርጋል - አምባሳደር መሃሙድ ዲሪር
ሐረር ሰኔ 5/2015 (ኢዜአ) - ሀገራዊ ምክክሩ ግጭቶችን በዘላቂነት በመፍታት በዜጎች መካከል የተሻለ ማህበራዊ ውል እንዲፈጠር ያደርጋል ሲሉ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር መሃሙድ ድሪር ገለጹ።
ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አጀንዳ ለማሰባሰብ፣ ስለሚከናወኑ ተግባራትና የውይይት ተሳታፊዎች መረጣ ላይ ከሐረሪ ክልል ነዋሪዎች ጋር ዛሬ በሐረር ከተማ እየመከረ ነው ።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር መሃሙድ ድሪር እንደገለፁት፤ ሀገራዊ ምክክሩ ግጭቶችን በዘላቂነት በመፍታት በዜጎች መካከል የተሻለ ውል የሚፈጥር ነው።
አለመግባባትን በማስቀረት የዲሞክራሲ ባህልን እንደሚያዳብር ገልጸው፤ በግጭቶች እና ጦርነቶች የተነሳ ከሚከሰተው ችግር መውጣት የሚቻለው በሀገራዊ ምክክር በመሆኑ ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ስራ መገባቱን አንስተዋል፡፡
በህዝብ መካከል አለመግባባት እንዲፈጠር የሚሰሩ አካላት መኖራቸውን ጠቁመው፤ ምክክሩ በህዝቦች መካከል መተማመን እንዲፈጠር የሚያደርግ መሆኑን አመልክተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በዜጎች መካከል የተሻለ ማህበራዊ ውል እንዲኖር እና ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ በሰላም ወጥቶ መግባት እና በሰላም መኖር ይፈልጋል ያሉት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም በበኩላቸው ሀገራዊ ምክክሩ ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ፋይዳ ያለው ጉዳይ እንደሆነ አስገንዝበዋል።
በመሆኑም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት የድርሻውን መወጣት እንደሚጠበቅበት አመልክተዋል።
ለዚህም እያዳንዱ ዜጋ እውነቱን በመነጋገር ለሚታዩ አለመግባባቶች መፍትሄ ማመንጨት እንደሚገባ ገልጸው፤ በአደባባይ እውነትን የመነጋገር ልምድ መዳበር እንዳለበት ተናግረዋል።
የሀረር ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ቶማስ ታደሰ ለሀገራዊ ምክክሩ በስኬት መጠናቀቅ ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው አንድነትን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ገልጸዋል።
በሀገራዊ ምክክሩ ሰላማዊ ኢትዮጵያ እንደምትፈጠር ያላቸውን እምነት ገልጸው፤ ለዚህም የድርሻቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
ሌላኛው የሀረር ከተማ ነዋሪ አቶ ከድር አህመድ የሀገራዊ ምክክሩ ዋና አላማ የግጭቶችን መንስኤ በመለየት በጋራ መፍታት መሆኑን በመጥቀስ፤ ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ በክልሉ የሚገኙ የማህበረሰብ ተወካዮች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ሌሎች ማህበራትም እየተሳተፉ ሲሆን የተሳታፊዎች ልየታ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡