በተለያዩ ተቋማት ተግባራዊ የተደረገው የህፃናት ማቆያ ለሠራተኞች ውጤታማነትና ለተቋማት የሥራ አፈጻጸም የላቀ አስተዋጽዖ እያበረከተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በተለያዩ ተቋማት ተግባራዊ የተደረገው የህፃናት ማቆያ ለሠራተኞች ውጤታማነትና ለተቋማት የሥራ አፈጻጸም የላቀ አስተዋጽዖ እያበረከተ ነው

አዲስ አበባ ሰኔ 5/2015 (ኢዜአ) ፦በተለያዩ ተቋማት ተግባራዊ የተደረገው የህፃናት ማቆያ ለሠራተኞች ውጤታማነትና ለተቋማት የሥራ አፈጻጸም የላቀ አስተዋጽዖ እያበረከተ መሆኑን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
በአዲስ አበባ በአብዛኛው የፌዴራል መንግሥት ተቋማት የህፃናት ማቆያ ማዕከላት ተገንብተው ወላጆች ዕድሜያቸው ከሦስት ወር እስከ አራት ዓመት ያሉ ህፃናትን አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑ ይታወቃል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አለሚቱ ኡሞድ፤ በተቋማት የልጆች ማቆያ ማዕከል በመኖሩ በተለይም ሴት ሠራተኞች ልጆቻቸውን በሚሰሩበት አካባቢ የሚያቆዩበትና ጡት የሚያጠቡበትን ምቹ ሁኔታ የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
ህፃናትም የወላጆቻቸውን ፍቅርና እንክብካቤ በቅርብ እንዲያገኙ በማስቻሉም ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ እያስገኘ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም በተለያዩ ተቋማት ተግባራዊ የተደረገው የህፃናት ማቆያ ለሠራተኞች ውጤታማነትና ለተቋማት የሥራ አፈጻጸም የላቀ አስተዋጽዖ እያበረከተ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
ከዚህ ውጤት በመነሳትም በቀጣይ ከፌደራል የመንግሥት ተቋማት ባለፈ በክልሎችም እንዲተገበር ለማድረግ የህፃናት ማዕከላትን የማቋቋም ሥራ ተጀምሯል ብለዋል።
በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች አገልግሎቱ ለህፃናት ምቹ እንዲሆን በማድረግ ረገድ የተለያዩ የማሻሻያ ሥራዎቸን እያከናወኑ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልጸዋል።
በመሆኑም በቀጣይ አገልግሎቱን ማስፋት፣ ምቹና ለህፃናት ተመራጭ እንዲሆን ሁሉም በትብብር መሥራት ይጠበቅበታል ብለዋል።
ከተቋማት የህፃናት ማቆያ ማዕከላት መካከል የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር (ኢንሳ) 180 ህፃናትን ተቀብሎ እየተንከባከበ መሆኑን የኢዜአ ሪፖርተር በሥፍራው ተገኝቶ ተመልክቷል።
በኢንሳ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ዳይሬክተር የምሥራች ፋሪስ፤ ማዕከሉ በ2010 ዓ.ም. ከ20 ያልበለጡ ህፃናትን ተቀብሎ ሥራ መጀመሩን አስታውሰዋል።
በየዓመቱ እየተስፋፋና እየተሻሻለ መጥቶ አሁን ላይ ከአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ ከፋይናንስ ኢንተለጀንስና ከሰላም ሚኒስቴር ተቋማት ሠራተኞች ጋር በድምሩ 180 ህፃናትን ተቀብሎ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
በማዕከላቱ ልጆች ውለው የሚሄዱበት ብቻ ሳይሆን በዕድሜያቸው ከፍ ያሉትን ፊደል እንዲለዩ በማድረግና ሌሎችም ፍላጎቶችን በማሟላት በስነ-ምግባር በጥሩ እንክብካቤ እንዲያድጉ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በገቢዎች ሚኒስቴር ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ የተቋቋመው የህፃናት ማቆያም ከ25 በላይ ህፃናትን በመቀበል አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን በሚኒስቴሩ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ዳይሬክተር ሰርካለም ሞገስ ገልጸዋል።
በኢንሳ ከአገልግሎቱ ተጠቃሚ ሰራተኞች መካከል ወይዘሮ ምሥራቅ ጌታቸው፤ በተቋማቸው የህፃናት ማቆያ አገልግሎት በመሰጠቱ ልጃቸውን በአቅራቢያ በማግኘታቸው ሥራቸውን በተረጋጋ መልኩ እንዲያከናውኑ ያስቻላቸው መሆኑን ገልጸዋል።
የገቢዎች ሚኒስቴር ሰራተኛ የሆኑት ወይዘሮ ትዕግስት ወንድይራድ፤ የህፃናት ማቆያ ማዕከላት በመኖሩ በብዙ መልኩ እኛንም ተቋሙንም የጋራ ተጠቃሚ ማድረግ ያስቻለ መልካም ጅምር ነው ብለዋል።
የህፃናት የቀን ማቆያዎችን ከማስፋፋትና ከማጠናከር አኳያ የፌደራል የመንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/2010 ዓ.ም ሁሉም የመንግሥት ተቋማት የህፃናት የቀን ማቆያን እንዲያቋቁሙ ያስገድዳል፡፡