ቀጥታ፡

የአንድነት ፓርክ እጽዋት ማዕከል በኢትዮጵያ ለብዝሃ ህይወት ጥበቃ አዲስ ምእራፍ የከፈተ ነው

አዲስ አበባ ሰኔ 05/2015 (ኢዜአ) የአንድነት ፓርክ እጽዋት ማዕከል በኢትዮጵያ ለብዝሃ ህይወት ጥበቃ አዲስ ምእራፍ የከፈተ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ሌሎች የእጽዋት ማእከላትን በተለያዩ አካባቢዎች በማስፋት የአገር በቀል እጽዋትን ጠብቆ ማቆየት እንደሚገባም ተጠቁሟል፡፡

በቅርቡ ተመርቆ ለእይታ ክፍት የሆነው የአንድነት ፓርክ እጽዋት ማእከል በኢትዮጵያ በተለያዩ ስነ-ምህዳር የሚበቅሉ እጽዋትን በአንድነት የያዘ ነው፡፡

በማዕከሉ ባለሙያ የሆኑት ወንድዬ ከበደ እንደሚሉት፤ ማዕከሉ በውስጡ ባለው "ግሪን ሃውስ" አማካኝነት ከውርጭ እስከ በረሃ ያለውን የኢትዮጵያ ስነ ምህዳር የያዘ ነው፡፡


 

በዚህም ማዕከሉ ከ230 በላይ የእጽዋት ዝርያዎችን የያዘ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

በኢትዮጵያ ከ6 ሺህ በላይ የእጽዋት ዝርያዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ መሰል ማዕከላትን በማስፋት አገር በቀል ዝርያዎችን መጠበቅ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የእጽዋት ማዕከሉ በውስጡ ከያዘቸው እጽዋት ዝርያዎች ባሻገር የዘር ባንክ እንዳለውም ነው ያብራሩት፡፡

በተጨማሪም የእጽዋቱ አጠቃላይ መረጃ በተደራጀ መልኩ በዲጂታል ስርዓት መሰነዱንም ባለሙያው ተናግረዋል፡፡

በማዕከሉ 15 የሚደርሱ ብርቅዬ የእጽዋት ዝርያዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ የማዕከሉ መገንባት እነዚህ ዝርያዎችን በምርምር አባዝቶ እንዳይጠፉ ለማድረግ ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡  

በመሆኑም እንደ አንድነት ፓርክ እጽዋት ማዕከል ያሉ ማዕከላትን በክልሎች በማስፋት ከሀገር አልፎ ዓለም አቀፋዊ ፋይዳ ያላቸው የእጽዋት ማዕከላትን መፍጠር እንደሚገባም ተናግረዋል።

በእጽዋት ማእከሉ ተማሪዎቻቸውን ይዘው ሲጎበኙ ያገኘናቸው መምህር ዓለም አሰፋ ፤ማዕከሉ ተማሪዎች በንድፍ ሀሳብ የሚያውቁትን በተግባር እንዲመለከቱና እንዲገነዘቡ እድል የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡


 

በተመሳሳይ ማእከሉን ሲጎበኙ ያገኘናቸው የቅድስተ ማሪያም ካቶሊክ ትምህርት ቤት የ3ተኛ ክፍል ተማሪ ፌቨን ሀብተማሪያም እና አሜን ሙሉቀን በማዕከሉ በክፍል ውስጥ በንድፍ ሀሳብ የሚያውቋቸውን እጽዋት በአካል ማየት መቻላቸውን ጠቁመዋል፡፡


 

በጉብኝታቸውም በየአካባቢያቸው የሚያገኟቸውን እጽዋትን መንከባከብ እንዳለባቸው መገንዘባቸውን ተናግረዋል፡፡

 

 

 

 

 


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም