ቀጥታ፡

በኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ ብረቶች ላይ የሚፈጸም ስርቆት የኃይል ስርጭቱ ላይ እንቅፋት ሆኗል - የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል

አዲስ አበባ ሰኔ 05/2015 (ኢዜአ)፡- በከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ ብረቶች ላይ የሚፈጸም ስርቆት የኃይል ስርጭቱን  እያስተጓጎለ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ገለጸ፡፡

በከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ ታወር ብረቶች ላይ የሚፈጸመውን ስርቆት ለመከላከል የብረት ማቅለጫ ድርጅቶች የሚኖራቸውን ሚና በተመለከተ ከዘርፉ ተዋንያን ጋር ውይይት እየተደረገ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማስተላለፊያ መስመሮችና የማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሀብታሙ ውቤ እንዳሉት፤ በከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ ብረቶች ላይ ስርቆት እየተፈጸመ ነው፡፡

በመሆኑም በእነዚህ ከፍተኛ ወጭ በሚያስወጡ የታወር ብረቶች ላይ የሚፈጸም ስርቆት ህብረተሰቡ በቂ ኃይል እንዳያገኝ እንቅፋት መሆኑን ጠቅሰው፤ ተቋሙንም ለአላስፈላጊ ወጭ እየዳረገው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የኤሌክትሪክ ታወር ብረቶች ላይ  የሚፈፀመውን ስርቆትን ለመከላከል የሁሉም ድርሻ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የታወር ብረቶች ላይ ስርቆት የሚፈፅሙ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንደሚገባም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም