ቀጥታ፡

የአፍሪካ-እሲያ የወጣቶች ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ ሰኔ 5/2015(ኢዜአ)፦ የ2023 የአፍሪካ-እሲያ የወጣቶች ፎረም "ጤናማና አቅም ያለው ወጣት ለዘላቂ ልማት" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።

በኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው የወጣቶች ፎረም ላይ ከተለያዩ የአፍሪካና እሲያ አገራት የተውጣጡ ወጣቶች እየተሳተፉ ነው።

በመረሃ-ግብሩ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፣ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደአ፣ የአፍሪካና እሲያ አገራት ዲፕሎማቶችና ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የመረሃ-ግብሩ ዋና አላማ የአፍሪካንና የእሲያ ወጣቶችን አንድ ላይ በማሰባሰብና በማሳተፍ በስራ ፈጠራ በቢዝነስ፣ በጤና፣ በከባቢያዊ አየር ጸባይ ለውጥ፣ በሰላም፣ በበጎ ፈቃደኝነት እና በሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ልምድ እንዲጋሩ በማድረግ ወጣቶችን ለማብቃት ታሳቢ ያደረገ መሆኑ ተገልጿል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ ወጣቶች በሀገራት የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና ማህበራዊ ተሳትፎ ላይ ቁልፍ ሚና ያላቸው መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም ወጣቶች በአመራር፣ በስራ ፈጠራ፣ በኢኮኖሚ፣ ሰላም በማስፈን ላይ ሁሉን አቀፍ ተሳትፎ እንዲኖራቸው መድረኩ ወሳኝ መሆኑን አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ የኢንዶኔዥያ አምባሳደር አል ቡስራ ባስኑር አፍሪካንና እሲያን በወጣቱ ሃይል ተሳትፎ ማስተሳሰር በአህጉራቱ መካከል ያለውን ሁሉን አቀፍ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሻግር እንደሚሆን እምነታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም