ቀጥታ፡

የፀሐይ ኃይልን በመጠቀም የከርሰ ምድር ውሃን ለመስኖ ለማዋል እየተተገበረ የሚገኘው የድሪም ፕሮጀክት ወደ ተለያዩ ክልሎች ለማስፋት ዝግጅት እየተደረገ ነው--የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ሰኔ 5/2015(ኢዜአ):- የፀሐይ ኃይል በመጠቀም የከርሰ ምድር ውሃን ለመስኖ ለማዋል እየተተገበረ የሚገኘው የድሪም(DREAM) ፕሮጀክት ወደ ተለያዩ ክልሎች ለማስፋት ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ የተመራ ቡድን በአርባ ምንጭ ዙሪያ እየተሰራ ባለው የድሪም ፕሮጀክት ላይ የመስክ ምልከታ አካሄዷል።

በፀሐይ ኃይል(ሶላር ኢነርጂ) አማካኝነት የከርሰ ምድር ውሃን ለመስኖ ልማት በመጠቀም ከ1 ሺህ 200 ሄክታር መሬት በላይ የሚያለማ በአራት ክልሎች በዘጠኝ አካባቢዎች እየተተገበረ እንደሚገኝ ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

በቀጣይ ፕሮጀክቱ ባልተጀመረባቸው ክልሎች ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።


 

በነዳጅ የሚሰሩ የውሃ ፓምፖች መጠቀም ከዚህ ቀደም የተለመደ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት በነዳጅ ዋጋ ንረት ምክንያት አዋጭ አለመሆናቸውን አንስተዋል።

በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲቲዩት በሲዳማ እና በደቡብ ክልሎች የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ አለሙ ተከተል በበኩላቸው የፕሮጀክቱ አላማ ከፀሐይ በሚገኝ ኃይል በመጠቀም የከርሰ ምድር ውሃን በማውጣት በዋናነት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን የሰብል ምርት በማምረት የሕብረተሰቡን የማምረት አቅም ማሳደግ መሆኑን አመልክተዋል።

በተጨማሪም በፕሮጀክቱ ከዋናው መስመር ኃይል ውጭ ያሉ ዜጎችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት  ላይ መስራቱን  ገልጸዋል።

 በአብነትም በአርባ ምንጭ ዙሪያ እየተሰራ ያለውን የድሪም ፕሮጀክት ግንባታ ከሚያስፈልጉ የ14 ጉድጓዶች የ10ሩ መጠናቀቁን ተናግረዋል።

ቀሪዎቹን በቀጣይ ሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ፤ ፍተሻና የሶላር ፓኔል ተከላ ስራ ጎን ለጎን እንደሚከናወን አስተባባሪው መግለጻቸውን የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

የፀሐይ ኃይል በመጠቀም የከርሰ ምድር ውሃን ለመስኖ ለማዋል እየተተገበረ የሚገኘው የድሪም ፕሮጀክት ጥቅምት 2015 ይፋ መደረጉ ይታወሳል።

ፕሮጀክቱ በደቡብ፣ ሲዳማ፣ አማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች በሙከራ ደረጃ በመተግበር ላይ ነው።

በ20 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር እየተተገበረ የሚገኘው ፕሮጀክት የዓለም ባንክ፣ የአውሮፓ የኢንቨስትመንት ባንክ እና የአፍሪካ ልማት ባንክ በአፍሪካ ዘላቂ ኢነርጂ ፈንድ አማካኝነት ወጪውን ይሸፍናሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም