ቀጥታ፡

የደቡብ ክልል የሰፖርት ዘርፉ እንዲያድግ ጠንካራ ድጋፍ እንደሚያድርግ ገለጸ

ሀዋሳ ሰኔ 4/2015 (ኢዜአ)፡- የደቡብ ክልል የሰፖርት ዘርፉ እንዲያድግ ጠንካራ ድጋፍ እንደሚያደርግ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር  ርስቱ ይርዳው ገለጹ።

በክልሉ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን ለተቀላቀሉት የአምበርቾ የሴቶችና የወንዶች እግርኳስ ቡድን የገንዘብና የአውቶብስ ሽልማት ከክልሉ መንግስት ተበርክቶላቸዋል።

በሽልማት ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው እንዳሉት የክልሉ መንግስት በስፖርቱ ዘርፍ ውጤት የሚያስመዘግቡና ወደ ፕሪሚየር ሊጉ የሚገቡ ቡድኖችን ለመሸለም የሚያስችል መመሪያ አዘጋጅቷል።

በዚህም መመሪያ መሰረት ከምድቡ አንደኛ ወጥቶ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለገባው የአምበርቾ ወንዶች እግር ኳስ ቡድን 150 ሺህ ብርና አንድ መለስተኛ አውቶቡስ መሸለሙን ገልጸዋል።

ሁለተኛ በመውጣት ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ለገባው የሴቶች እግርኳስ ቡድን የ100 ሺህ ብርና በተመሳሳይ አውቶቡስ መሸለሙንም አቶ ርስቱ ተናግረዋል።

በቀጣይም የክልሉ መንግስት በክልሉ ስፖርት ይበልጥ እንዲጠናከር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የክልሉ ስፖርት ቢሮ ሀላፊ አቶ ዘርይሁን እሸቱ በበኩላቸው በክልሉ የስፖርት ዘርፉን የበለጠ ለማጠናከር ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው የማድረግ ስራ ላለፉት ዓመታት ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል።

በዚህም በርካታ ክለቦችን በፕሪሚየር ሊጉ እንዲሳተፉ ከማድረግ ባለፈ ስፖርተኞች ለብሄራዊ ቡድን በማስመረጥም በኩል ክልሉ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል።

ከክልላችን ዞኖች የከምባታ ጠምባሮ ዞን በእግር ኳስ ዘርፍ በኢትዮጵያ ደረጃ ድንቅና ተጫዋቾችን በማሳተፍ የማይረሳ ሚና እየተወጡ አንደሚገኙ ጠቁመዋል።

የአምበርቾ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን ተጫዋች የሆነችው ምጽዋት ጸጋዬ እንዳለችው በከፍተኛው ሊግ በነበራቸው ቆይታ ለቡድኗ አራት ጎል እንዳስቆጠረችና አሁን በፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ ግብ አግቢ ለመሆን የበለጠ እንደምትሰራ ገልጻለች።

በክልሉና በዞኑ መንግስትና ህዝብ በተደረገላቸው አቀባበልና ባገኙት ሽልማትም ደስታ እንደተሰማት ተናግራለች።

የወንዶቹ ቡድን አንበል የሆነው እንዳለ ዮሀንስ በበኩሉ በሱፐር ሊጉ በነበራቸው ቆይታ እንድም ጊዜ ሽንፈት እንዳላጋጠማቸው ገልጾ በሚቀጥለው አመት በፕሪሚየር ሊጉ ይህን በመድገም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የሚጠበቅበትን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።

በሱፐር ሊጉ ሶስት ጎሎችን እንዳስቆጠረና በቀጣይ በፕሪሚየር ሊጉ የጎሉን መጠን በማሳደግ ቡድኑን ጠንካራ ተፎካካሪ ለማድረግ መዘጋጀቱንም ጠቁሟል።

ወላይታ ድቻ፣ ሀድያ ሆሳዕና፣ ወልቂጤና አርባምንጭ ከነማን በወንዶች እንዲሁም ጌዴኦ ይርጋጨፌና አርባምንጭ ከነማ በሴቶች በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክልሉን ወክለው የሚሳተፉ ቡድኖች መሆናቸውን ተገልጿል። 

የአምበርቾ ዱራሜ የእግርኳስ ቡድን ትናንት ምሽት በክልሉ ከተሸለመው የገንዘብና አውቶቡስ ሽልማት በተጨማሪ በዞኑ አስተዳደር ለእያንዳንዳቸው ተጫዋቾች ቤት መስሪያ ቦታ መሸለማቸው የሚታወስ ነው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም