ቀጥታ፡

የቱሪዝም ኢንዱስትሪው የሚጠበቅበትን ያህል ገቢ እንዲያመነጭ ሊሰራ ይገበል - የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት 

ጂንካ ሰኔ 4/2015(ኢዜአ)፡- የቱሪዝም ኢንዱስትሪው በሚጠበቅበት ልክ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዲያስገኝ መሰራት እንዳለበት የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ገለጸ።

11ኛው ዓመታዊ የቱሪዝም ጥናትና ምርምር ጉባኤ "ብዘሃነትና ዘላቂ የቱሪዝም ልማት ለስራ እድል ፈጠራ'' በሚል መሪ ሀሳብ  በጂንካ ከተማ ተካሂዷል።

የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ በዚሁ ወቅት እንዳሉት መንግስት ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው በሰጠው ትኩረት የአገር ውስጥና የውጭ አገራት ጎብኚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ነው።

ኢንዱስትሪው ለዜጎች የስራ እድል እየፈጠረ ቢሆንም ከሌሎች አገራት ልምድና ተሞክሮ አንፃር ሲታይ ግን ዘርፉ በሚጠበቅበት ልክ አገራዊ ጥቅም እያስገኘ አለመሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም አገሪቱ ያላት እምቅ የቱሪዝም ሀብት ኢኮኖሚን እንዲያመነጭ በማድረግ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ማሳደግና ለዜጎች ሰፊ የስራ እድል መፍጠር እንደሚገባም ተናግረዋል።

በአገሪቱ  የብዘሃ-ባህልና የቱሪስት መስህቦች መገኛ ከሆኑ ስፍራዎች አንዱ የደቡብ ኦሞ ዞን ነው ያሉት ደግሞ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ኩሴ ጉድሼ ናቸው።





 

በደቡብ ኦሞ ያለውን እምቅ የቱሪዝም ሀብት ለማህበረሰብ ልማት ለማዋልና ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማሳደግ ዩኒቨርስቲው በትኩረት እየሰራ መሆኑን ዶክተር ኩሴ ገልጸዋል።

ከጉባኤው ተሳታፊዎች መካከል የኢትዮጵያ የሆቴል ባለሙያዎች ተወካይ አቶ ክፍሉ ገብረጊዮርጊስ በሰጡት አስተያየት በአገሪቱ በርካታ ከዓለም ተወዳዳሪ የሆኑ የቱሪስት መስህቦች ቢኖሩም ከዘርፉ የሚገኘው ሀብት ውስን መሆኑ እንዳስቆጫቸው ተናግረዋል።

ከዘርፉ የሚገኘውን አገራዊ ጥቅም ለማሳደግም ሁሉም በቁጭት ሊነሳ እንደሚገባ ነው የገለፁት።

የቱሪስት ፍሰቱን ለመጨመር በተለይ በሆቴልና ቱሪዝም አገልግሎት የተሰማሩ ባለሙያዎች አካባቢያቸውን በሚገባ በማስተዋወቅና ለጎብኚዎች ጥሩ መስተንግዶ በማድረግ የአምባሳደርነት ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አቶ ክፍሉ አሳስበዋል።

እንደ ደቡብ ኦሞ ባሉ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎች ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች አለመኖራቸው የቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ እያሳጠረ እንደሚገኝ የገለፁት ደግሞ የአዲስ አበባ የሆቴል ባለቤቶች ማህበር ፕሬዝዳንት ወይዘሮ አስቴር ሰለሞን ናቸው።

በመድርኩ ላይ  በነዚህ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎች ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎችን በመገንባት የድርሻቸውን እንዲወጡ በቀረበላቸው ጥሪ መሰረት ከማህበሩ አባላት ጋር በመምከር ምላሽ እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

ጉባኤው በተለያዩ ተመራማሪዎች የተሰሩ የጥናትና ምርምር ስራዎች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል።

❝በቱሪዝም መስክ ያሉ እድሎች እና ፈተናዎች❞ በሚል ፅንሰ-ሀሳብ በቀረበ አንድ ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት ተቀዛቅዞ የነበረው የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ከዚያ ወዲህ መነቃቃት ማሳየቱም ተመላክቷል።

ነገር ግን በሆቴሎችና በመስህብ ስፍራዎች በቂ የሰለጠነ የሰው ሃይል አለመኖር፣ በአብዛኛው የመስህብ ስፍራዎች የመንገድ መሰረተ ልማት አለመሟላት እና ሌሎችም እንደ ተግዳሮት የተነሱ ሀሳቦች ናቸው።

እነዚህንም ችግሮች ለመቅረፍ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የክሂሎት ስልጠና የሚሰጡ የትምህርትና ስልጠና ተቋማትን አቅም በመገንባት በዘርፉ ብቁ የሰው ሀይል ማፍራት እንዲችሉ መስራት እንደሚገባም ተነስቷል።

የመንገድ መሰረተ ልማት ከሟሟላት ጋር ተያይዞ የሚመለከታቸው ተቋማት ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት እንዲሰሩም ተጠይቋል።

በጉባኤው የፌዴራል እና የክልል የዘርፉ አስፈጻሚዎች እና ባለድርሻ አካላት ፣የሆቴልና ቱሪዝም ድርጅት ተወካዮች ፣ የትምህርት ስልጠና ተቋማት፣ የሙያ ማህበራት እና የተለዩ ጥናት አቅራቢዎች ተሳትፈዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም