ቀጥታ፡

 መንግስት የአገር በቀል እውቀቶችን መሰረተ ያደረገ እድገት ለማስመዝገብ በሚያደርገው ጥረት የዩኒቨርሲቲዎች ሚና የላቀ ነው- አቶ አደም ፋራህ

ባህርዳር ሰኔ 04/2015   (ኢዜአ) መንግስት የአገር በቀል እውቀቶችና እሴቶችን መሰረተ  ያደረገ እድገት ለማስመዝገብ  በሚያደርገው ጥረት የዩኒቨርሲቲዎች ሚና የላቀ መሆኑን   የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት  አደም ፋራህ ገለፁ።

የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ለአንድ ዓመት ሲያከብረው የቆየው 60ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የመዝጊያ ስነ-ስርዓት በተለያዩ ዝግጅቶች በዩኒቨርሲቲው ስታዲየም አክብሯል።

የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንትና የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አደም ፋራህ በመዝጊያ ስነ-ስርአቱ ላይ እንደገለፁት መንግስት የዩኒቨርሲቲዎችን የራስ ገዝ አሰራርና ተቋማዊ ነፃነትን ለማስፈን በትኩረት እየሰራ ነው።

ይህም ተቋማዊ ነፃነትን ከማረጋገጥ ባሻገር የፋይናንስና የውስጥ አስራሮችን በማደራጀት ከውጭና ከአገር ውስጥ ሃብት በማመንጨት ለመተግበር የሚያስችላቸው ነው ብለዋል።

በተለይም መንግስት በሁሉም ዘርፎች እየተገበረ የሚገኘው የአገር በቀል እውቀቶችና እሴቶች ላይ የተመሰረተ የአገር እድገትና የማህበረሰብ ለውጥ ለማሳካት የዩኒቨርሲቲዎች ሚና የላቀ መሆኑን አስረድተዋል።

የባህርዳር ዩኒቨርሲቲም በ2022 ዓ.ም በአፍሪካ ከሚገኙ ግንባር ቀደም የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ለመሆን እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ይሄን ለማሳካትም በአገር በቀል እውቀትና እሴት ላይ ተመስርቶ እንዲሰራ አሳስበዋል።

ባለፈው አንድ አመት በዓሉን ሲያከብርም ሃሳብ በማመንጨት፣ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅና ሌሎች ተግባራትን በማከናወን አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።


 

የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በመማር ማስተማር፣ በምርምርና ማህበርሰብ አቀፍ አገልግሎት ለአገር እድገትና ብልፅግና ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ገልፀዋል።

በተለይም በመማር ማስተማር ዘርፍ ከ200ሺህ በላይ የተማረ የሰው ሃይል በማፍራት አስተዋፅኦ ማበርከቱን ጠቁመው፤ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ሽግግር ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ ውጤታማ ለመሆን በቅቷል ብለዋል።

በዚህም ዘንድሮ በአፍሪካ በሚገኙ 70 ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ መካተቱን ገልፀው፤ በቀጣይም በምርጥ የአፍሪካ ምርምር ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ ለመሆን መንገዱን የሚያመቻችለት መሆኑን አስረድተዋል።

የ60ኛ ዓመት በዓሉን ሲያከብርም ከተለመደው አሰራር በመውጣትና ሰባት ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ ከባለሃብቶችና ተቋማት ጋር በመተባበር ለባህርዳር ከተማ እድገት መፋጠንም አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ ማተኮሩ የተለየ ያደርገዋል ብለዋል።.

ከሚተገበሩት ፕሮጀክቶች ውስጥም የባህርዳር ልዩ የሞዴል ትምህርት ቤት፣ የጉዶ ባህር ሰው ሰራሽ ሃይቅና አረንጓዴ ልማት፣ አብርሆት የባህርዳር የህዝብ ቤተ መፃህፍት እንዲሁም የባህርዳር የብስክሌት ፕሮጀክትን ግንብቶ ለማስረከብ ባለሃብቶችና ድርጅቶች ቃል በመግባት ወደ ተግባር በመግባት ላይ ናቸው ብለዋል።


 

ቀሪዎቹ የአባይ ማራቶን ፕሮጀክቶችን ጨምሮ ዩኒቨርሲቲው ከሌሎች አካላት ጋር በመተባበርና በመገንባት በባህርዳር ከተማ እድገት የ60ኛ ዓመቱን አሻራውን ያስቀምጣል ብለዋል።

በመዝጊያ ስነ ስርአቱ ላይ የተለያዩ አገራት ኤምባሲዎች፣ ተቋማትና ድርጅቶች እንዲሁም የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን ጨምሮ የሚዲያ ተቋማትና ሌሎች አካላት የእውቅና ሽልማት ተሰጥቷቸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም