በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማ ክልል ማስተባበሪያ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ዴሞክራሲን ለማጎልበት እያከናወነ ያለው ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይግባል - ኢዜአ አማርኛ
በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማ ክልል ማስተባበሪያ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ዴሞክራሲን ለማጎልበት እያከናወነ ያለው ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይግባል
ሀዋሳ ሰኔ 4/2015 (ኢዜአ)፡- በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማ ክልል ማስተባበሪያ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ዴሞክራሲን ለማጎልበት እያከናወነ ያለው ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለጸ።
በምክር ቤቱ የዴሞክራሲያዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማ ክልል ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤትና በህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤትን የስራ እንቅስቃሴ ገምግሟል።
ከግምገማው በኋላ የቋሚ ኮሚቴው ቡድን መሪ ወይዘሮ ዘሃራ ቢፍቱ ለኢዜአ እንዳሉት በሁለቱ ተቋማት ዴሞክራሲን ለማጎልበትና በህዝብ ላይ የሚደርስን በደል ከማስቀረት አንጻር እየተከናወነ ያለው ተግባር የሚበረታታ ነው።
በተለይም በምርጫ ቦርድ የሲዳማ ክልል ማስተባበሪያ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በስነ ዜጋና ዴሞክራሲ ዙሪያ ለህብረተሰቡ እየሰጠ ያለው የግንዛቤ ማጎልበቻ ትምህርት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያዩ ተጽዕኖ እንዳይደርስባቸው በቦርዱ ጽህፈት ቤት ቦታ ተሰጥቷቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ እነሱ ባሉበት መካሄዱ የፖለቲካ ምህዳሩን ከማስፋት አንጻር ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለውም ለአብነት አንስተዋል።
በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማ ክልል ማስተባበሪያ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስተባባሪ አቶ ፍሬው በቀለ በበኩላቸው ቋሚ ኮሚቴው በጽህፈት ቤቱ ተገኝቶ "በአሰራራችን ዙሪያ ከእኛ ጋር መወያየቱ ለወደፊቱ በስራችን እንድንጠነክር ጉልበት ይሰጠናል" ብለዋል።
በተለይም ቋሚ ኮሚቴው ባቀረብንለት ሪፖርት መሰረት በቀጣይ የመራጮችን ትምህርት ለማስፋፋት በትኩረት እንድንሰራና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅታችንን እንድናጠናክር የሰጠን አቅጣጫ ጠቃሚ ነው ብለዋል።
እኛም ከቢሮ አደረጃጀት አንጻርና ለቀጣይ ምርጫ በምናደርገው ቅድመ ዝግጅ ዙሪያ የሰጡንን አስተያየት በመቀበል ተግባራዊ እናደርጋለን ብለዋል።
ለስራችን ቅልጥፍና በዋናነት ከዴሞክራሲ ተቋማት ጋር በተለይም ከዕምባ ጠባቂ ተቋም፣ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትና ሌሎች አካላት ጋር የጋራ አሰራር በመፍጠር በቅንጅት መስራት እንዳለብን ከቋሚ ኮሚቴው የተሰጠን አስተያየት ነው ብለዋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በህዝብ ላይ የሚደርሱ በደሎችንና በአስፈጻሚ አካላት የሚደርስ ተጽዕኖን ለመከላከል እያከናወነ ያለው ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።