የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 28ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 28ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ
አዲስ አበባ ሰኔ 4/2015 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 28ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይደረጋሉ።
በመርሐ-ግብሩ መሰረት ወልቂጤ ከተማ ከመቻል ጋር ከቀኑ 9 ሰአት ላይ ይጫወታሉ።
በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ወልቂጤ ከተማ በ33 ነጥብ 14ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኝ ሲሆን መቻል በ34 ነጥብ 12ኛ ደረጃን ይዟል።
ወልቂጤ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች በሁለቱ አሸንፎ በአንዱ ተሸንፎ በሁለቱ አቻ ወጥቷል።
በአንጻሩ መቻል ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። በሁለቱ ተሸንፏል በሁለቱ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር ባደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ መለያየታቸው ይታወሳል።
በ28ኛ ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ-ግብር የመጨረሻው ጨዋታ በፋሲል ከነማ እና ኢትዮጵያ መድን መካከል ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ይደረጋል።
በደረጃ ሰንጠረዡ ፋሲል ከነማ በ38 ነጥብ 7ኛ ሲሆን ኢትዮጵያ መድን በ48 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ኢትዮጵያ መድን ካለፉት አምስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች ሁለቱን አሸንፎ በተመሳሳይ በሁለቱ ሲሸነፍ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል።
ተጋጣሚው ፋሲል ከነማ በበኩሉ ባለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ ተሸንፏል። ሁለት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ያደረጉት ጨዋታ ያለ ምንም ግብ በአቻ ውጤት መጠናቀቁ የሚታወስ ነው።
ከዛሬ ጨዋታዎች በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በኮትዲቭዋር አስተጋጅነት በሚካሄደው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ከማላዊ ጋር ሰኔ 13 /2015 ለሚያደርገው ጨዋታ ዝግጅት የፕሪሚየር ሊጉ ውድድር እንደሚቋረጥ የሊጉ የውድድር እና ስነ ስርዓት ኮሚቴ አስታውቋል።
በተያያዘም ትናንት በተደረገ የ26ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ባህር ዳር ከተማ ሁለት አቻ ተለያይተዋል።