በኢትዮጵያ አዘጋጅነት በተካሄደው አፍሪካ ዞን አራት የጎልፍ ስፖርት ሻምፒዮና በኬንያ ሻምፒዮንነት ተጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ አዘጋጅነት በተካሄደው አፍሪካ ዞን አራት የጎልፍ ስፖርት ሻምፒዮና በኬንያ ሻምፒዮንነት ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ ሰኔ3/2015(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ አዘጋጅነት በተካሄደው አፍሪካ ዞን አራት የጎልፍ ስፖርት ሻምፒዮና በኬንያ ሻምፒዮንነት ተጠናቀቀ።
በሻምፒዮናው ዩጋንዳ ሁለተኛ ሩዋንዳ ሶስተኛ ደረጃ የያዙ ሲሆን ኢትዮጵያ በአራተኛ ደረጃ እንዲሁም የመጨረሻውን ደረጃ ታንዛኒያ ይዛ ውድድሩ ተጠናቋል ።
የአፍሪካ ዞን አራት የጎልፍ ሻምፒዮና በአዲስ አበባ በሚገኘው የጦር ኃይሎች ጎልፍ ክለብ ከግንቦት 29 ጀምሮ ሲካሄድ ቆይቷል ።
በመርሃ ግብሩ ማጠናቀቂያ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣የአፍሪካ ጎልፍ ኮንፌደሬሽን ፕሬዚዳንት ጆንሰን ኦሞሎን ጨምሮ የተለያዩ እንግዶች ተገኝተዋል ።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ሻምፒዮናው በኢትዮጵያ በመዘጋጀቱ ልምድና ተሞክሮ የተገኘበት እንደነበር ገልጸዋል ።
ስፖርቱን ለማስፋፋት በርካታ ተግባራት ማከናወን እንደሚጠይቅ ያየንበት ነበርም ብለዋል።
ከውድድሩ ጎን ለጎን ከአፍሪካ ጎልፍ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ጋር ስፖርቱን በኢትዮጵያ ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ማድረግ መቻላቸውንም ገልጸዋል ።
የአፍሪካ ጎልፍ ኮንፌደሬሽን ፕሬዚዳንት ጆንሰን ኦሞሎ ውድድሩ በተሳካ መልኩ መጠናቀቁን አስታውቀዋል ።
ስፖርቱን በኢትዮጵያ ለማሳደግ መሰል ውድድሮች በማዘጋጀት ማጠናከር ይገባል ነው ያሉት ።
የጎልፍ ስፖርት በአፍሪካ ለማሳደግ መሰል ውድድሮች ማጠናከርና በጋራ መስራት ይገባልም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ጎልፍ ስፖርት አሶሴሽን ፕሬዝዳንት ተሾመ ሞሲሳ ውድድሩ ከዚህ በፊት በሌሎች ሀገራት ከነበሩት የአፍሪካ ሪጅን አራት ውድድሮች በተለየ ድምቀትና ስኬት መጠናቀቁን ገልጸዋል ።
በውድድሩ ወቅት ተሳታፊ ስፖርተኞች በጨዋታ ወቅት ያሳዩት ስፖርታዊ ጨዋነትና አፍሪካዊ ወንድማማችነት ስሜት የታየበት ነበር ብለዋል።