ቀጥታ፡

ባለፉት ሶስት ዓመታት የሎጂስቲክስ ዘርፉን ለማሻሻል በተከናወኑ ስራዎች 5 ቢሊዮን ብር የሎጂስቲክስ ወጪ ማዳን ተችሏል

አዲስ አበባ ሰኔ 3/2015(ኢዜአ)፡- ባለፉት ሶስት ዓመታት የሎጂስቲክስ ዘርፉን ለማሻሻል በተከናወኑ ስራዎች 5 ቢሊዮን ብር የሎጂስቲክስ ወጪ ማዳን መቻሉን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ ዶክተር አለሙ ስሜ ገለጹ።

"የሎጅስቲክስ ብቃት እና የተቋማት ቅንጅት ለዘላቂ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን" በሚል መሪ ሀሳብ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ ዛሬ በአዳማ ተካሂዷል።

በመድረኩ ዘርፉ የሚመለከታቸው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ኃላፊዎች፣ የክልል ምክትል ርዕሳነ መስተዳደሮች፣ የትራንስፖርት፣ የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር አለሙ ስሜ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን የገቢና ወጪ ንግድን ለማስተናገድ የሚያስችሉ በርካታ የልማት ስራዎች ተከናውነዋል።

ባለፉት ሶስት ዓመታት በብሔራዊ ሎጂስቲክስ ስትራቴጂ በመመራት ዘርፉን ለማሻሻል በተደረጉ ጥረቶች አበረታች ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።

በውስን አካላት ተይዘው የነበሩ የአገልግሎት ዘርፎችን ክፍት በማድረግና ቅንጅታዊ አሰራርን በማስፈን 5 ቢሊዮን ብር የሎጂስቲክስ ወጪን ማስቀረት መቻሉን ጠቁመዋል።

በትግበራ ሂደት ውስጥ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በመለየት በቀጣይ ዘርፉን ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር አብዱልበር ሸምሱ በበኩላቸው፤ ባለስልጣኑ በዘርፉ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱን ተናግረዋል።

ባለስልጣኑ የሎጂስቲክስ ዘርፍን በማገዝ ረገድ  የተለያዩ ችግር ፈቺ ጥናቶችን በማካሄድ ላይ መሆኑን ጠቅሰው፤ ጥናቶቹ ተጠናቅቀው ወደ ስራ ሲገቡ የዘርፉን ማነቆ መፍታት እንደሚያስችሉም አመላክተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ የክልል ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ቢሮ ኃላፊዎች ለዘርፉ የበለጠ ማደግ የጋራ ግንዛቤን ማሳደግና ቅንጅታዊ አሰራርን  ማጠናከር ተገቢ እንደሆነ ገልጸዋል።

በየክልሎቹ ችግር ፈቺና ቀልጣፋ የአሰራር ስርዓትን በመዘርጋት ሀገራዊ የሎጂስቲክስ  አቅምን በሚፈለገው ልክ ለማድረስ የበኩላቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም