ቀጥታ፡

የሀገር አንድነት የሚፀናውና ብልጽግና የሚረጋገጠው በፈጠራ ስራ አዕምሮ የዳበረ ትውልድ መገንባት ሲቻል ነው- ዶክተር ዘላለም ሙላቱ

አዲስ አበባ ሰኔ 3/2015(ኢዜአ)፡- የሀገር አንድነት የሚፀናውና ብልጽግና የሚረጋገጠው በፈጠራ ስራ አዕምሮ የዳበረ ትውልድ መገንባት ሲቻል ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ ገለጹ። 

"ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ልዩ ትኩረት በመስጠት የሀገራችንን ብልፅግና እናረጋግጣለን" በሚል መሪ ሃሳብ ለሶስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው 8ኛው ከተማ አቀፍ የሳይንስና ፈጠራ ስራ አውደ-ርዕይ ተጠናቋል።


 

በማጠቃለያ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ እንደገለጹት፤ አውደ ርዕዩ በሳይንስና ፈጠራ ስራዎች እውቀት ያላቸው መምህራንና ተማሪዎች የተወዳደሩበትና ልምድ የተለዋወጡበት ነበር።

የሳይንስና ፈጠራ ስራዎች ከሚበረታቱባቸው መድረኮች መካከል አንዱ መሆኑን በማንሳት፤ የፈጠራ ባለቤቶችን በማስተዋወቅ ችግር ፈቺ ስራዎቻቸውን ተግባር ላይ እንዲያውሏቸው  ያግዛቸዋል ብለዋል።

ትምህርት ቢሮ ይህን በመገንዘብ ተማሪዎች ተሰጧቸውን የሚያወጡባቸው የተለያዩ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ገልጸው በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ተማሪዎች በታዳሽ ኃይል የሚሰራ የችግኝ ማፍያና ማጠጫ ማሽን፣ ማየት የተሳናቸው በጉዞ ላይ ለአደጋ እንዳይጋለጡ የሚያደርግ ቴክኖሎጂ፣ ያለ ኢንተርኔት የሚተገበር ዲጂታል የተማሪዎች አቴንዳንስ መቆጣጠሪያ ማሽን ፈጠራዎች መስራታቸውን ጠቅሰዋል።

በቀጣይም የፈጠራ ስራዎቻቸውን አዳብረው ጥቅም ላይ ለማዋል እንደሚሰሩ ተናግረዋል።


 

በአውደ ርዕዩ የማጠቃለያ ፕሮግራሙ ላይ የተሻለ የፈጠራ ስራ ይዘው ለቀረቡ ተማሪዎችና መምህራን እውቅና ተሰጥቷል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም