የምስራቅ ኢትዮጵያ ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ቢሮና ካምፕ በድሬዳዋ ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ - ኢዜአ አማርኛ
የምስራቅ ኢትዮጵያ ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ቢሮና ካምፕ በድሬዳዋ ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ
ድሬዳዋ ሰኔ 3 /2015(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የምስራቅ ኢትዮጵያ የፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ቢሮና ካምፕን ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ።
የመሠረት ድንጋዩን በጋራ ያስቀመጡት የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ህብረት ፕሬዝዳንትና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤልና የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ናቸው።
ኮሚሽነር ጀነራሉ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር፤ ከ676 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የሚገነባው ዘመናዊ የፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ቢሮ እና ካምፕ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ብለዋል።
ይህም የፌደራል ፖሊስ ከምስራቅ የሀገሪቱ ክፍል የፀጥታ አካላት ጋር ተቀናጅቶ እያከናወነ የሚገኘውን የሰላም እና ፀጥታ የማስጠበቅ ስራ ለማጠናከር እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
በተለይ ድሬዳዋ ዘመናዊ የንግድ እና የኢንቨስትመንት መናኸሪያ ለማድረግ በፌደራል መንግስትና በአስተዳደሩ እየተካሄዱ የሚገኙ ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎች በተሳካ መንገድ ዳር እንዲደርሱ ግንባታው ወሳኝ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል ።
የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በበኩላቸው፤ የፌደራል ፖሊስ በድሬዳዋ ላይ የሚያካሂደው ግንባታ በምስራቅ የሀገሪቱ ክፍል የተጀመረውን የተቀናጀ ሰላም እና ፀጥታ የማስከበር ስራ ለማጠናከር እንደሚያስችል ገልጸዋል።
አስተዳደሩ ለግንባታው ፕሮጀክት አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ በታሰበለት ጊዜ እና ጥራት እንዲጠናቀቅ የድርሻውን እንደሚወጣ አስታውቀዋል።
ግንባታውን በተቀመጠው ጊዜ እና ጥራት አጠናቀው ተቋሙ ለታሰበለት ሀገራዊ ዓላማ እንዲውል በትጋት ይሰራል ያሉት ደግሞ የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ሰለሞን ደመቀ ናቸው።
የግንባታውን የመሠረት ድንጋይ በማስቀመጡ ሥነ-ሥርዓት ላይ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ከፍተኛ ኃላፊዎች የድሬዳዋ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች እና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ሆነዋል።