ኢትዮጵያ ያላትን ፀጋ አሟጦ መጠቀም የሚያስችል ጠንካራ የሥራ ባህል በመገንባት የአገሪቱን ብልጽግና ማረጋገጥ እንደሚገባ ተጠቆመ

133

አዲስ አበባ ሰኔ 3/2015(ኢዜአ) ኢትዮጵያ ያላትን ፀጋ አሟጦ መጠቀም የሚያስችል ጠንካራ የሥራ ባህል በመገንባት የአገሪቱን እድገት ማስቀጠልና ብልጽግናዋን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተጠቆመ።

"የመደመር ጉዞ" በሚል መሪ ኃሳብ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን የመደመር እሳቤ መጻሕፍትን መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት/ኢዜአ/ በቢሾፍቱ ከተማ ውይይት አካሂዷል።


 

ውይይቱ መደመር የሥራ ባህልና ዕይታን በመለወጥ የሚኖረው ፋይዳ የሚዳስሱ ኃሳቦች የተንሸራሸሩበት ሲሆን፤ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችና ሌሎች አካላት ተሳትፈዋል።

በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የአገር ውስጥ ሥራ ሥምሪት ማስፋፊያ ኃላፊ ደጀኔ በቀለ፤ ሦስቱም የመደመር እሳቤዎች በኢትዮጵያ የልማት ዘርፎች ውጤት እንዲመዘገብ እያስቻሉ መሆኑን ተናግረዋል።

ተቋማቸው የፈጠራ ኃሳብ ማበልጸጊያ ማዕከል እየገነባ መሆኑን ጠቁመው፤ የመደመር እሳቤዎች የሥራ ባህልን ከማሻሻል ጋር ከፍተኛ ቁርኝት እንዳላቸው ገልጸዋል።

በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የሲቪል ሰርቪስ ሕጎች ዴስክ ኃላፊ መስፍን ረጋሳ በበኩላቸው፤ በሰው ኃብት ልማትና አስተዳደር ሥርዓቱን ለማብቃት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ሁሉም ዜጋ የአገልጋይነት መንፈስ በመላበስ ተቆጥሮ የተሰጠውን ሥራ በብቃት በመፈጸም ለአገር እድገትና ልማት በትጋት መሥራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።


 

የመድረኩ ተሳታፊና አንጋፋው የጥበብ ሰው አርቲስት ደበበ እሸቱ፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሦስቱ የመደመር እሳቤ መጻሕፍት ለአገሪቱ ቀጣይ አቅጣጫ አመላካች የመፍትሔ ኃሳብ የያዙ መሆናቸውን ተናግሯል።

በእርሻ ኢንቨስትመንት አልሚ ባለኃብቷ በረከት ወርቁ በኢትዮጵያ በግብርና ኢንቨስትመንት ሥራ በስፋት መሰማራት እንደሚገባ ተናግራለች።

አገራችን በምትመች መልኩ እንገንባት የምትለው በረከት የስደት ኃሳብን በመተው ኢትዮጵያ ያላትን በቂ ሃብት አልምቶ መጠቀም የሚያስችል የሥራ ባህል ተነሳሽነት መፍጠር ያስፈልጋል ብላለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ በበኩላቸው፤ የመደመር እሳቤ የሚቆም ሳይሆን ሂደት ነው፤ እሳቤው ቀጣይ አቅጣጫ ለማመላከት ያስችላል ብለዋል።


 

የውጭ እሳቤዎች በኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ተጽዕኖ እንዳላቸው ጠቁመው፤ የመደመር እሳቤዎች አገር የሚገጥማትን ችግር በአገር በቀል እውቀት መፍትሔ ለመስጠት ፋይዳ እንዳላቸው ገልጸዋል።

በውይይቱ ላይ የመደመር እሳቤ የያዛቸው መልካም ዕድሎች፣ በሂደቱ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና መፍትሔ አመላካች ጉዳዮችን በሚዳስሱ ኃሳቦች ላይ ምክክር ተደርጓል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች የኢትዮጵያ አየር ኃይል በሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ያከናወናቸውን የለውጥ ሥራዎች ጎብኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም