ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው ዘርፍ ወደ አዲስ ምዕራፍ እየተሸጋገረች ነው- የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ ሰኔ 3/2015(ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ስጋትን ወደ ዕድል በመቀየር በኢኮኖሚው ዘርፍ ወደ አዲስ ምዕራፍ በመሸጋገር ላይ መሆኗን  የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ገለጹ፡፡  

ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ባለፉት ዓመታት በተመዘገቡ ኢኮኖሚያዊ ስኬቶችና ሌሎች ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ነው።

በመግለጫቸውም መንግስት ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከነጠላ ዘርፍ ወደ ብዝኃ ዘርፍ የምጣኔ ሀብት ዕድገት መቀየር መቻሉን ተናግረዋል።

በዚሀም በገጠር የግብርና ልማት ስትራቴጂ ላይ ያተኮረውን የልማት እንቅስቃሴ በመቀየር በሁሉም ዘርፎች ምርታማነትን በማሳደግ እና ሀገራዊ የጥቅል ምርትን በመጨመር ጫናዎችን መቋቋም የሚችል የኢኮኖሚ ዕድገትን ማስመዝገቡን ገልጸዋል፡፡  

የብዝኃ ዘርፍ ኢኮኖሚ ስርዓቱ የግብርና፣ የኢንዱስትሪ፣ የማዕድን፣ የቱሪዝም እና ዲጂታል ዘርፎችን በማስተሳሰር ሁለንተናዊ የልማት አቅጣጫን እየተተገበረ ነው ብለዋል።

መንግስት በመጀመሪያው ምዕራፍ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የመፍጠር አቅምን በማሳደግ ችግሮችን ተቋቁሞ ቀጣይነት ያለው ዕድገት ማረጋገጥ መቻሉን ተናግረዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን በመቋቋም እንዲሁም ስጋቶችን ወደ ዕድል በመቀየር በኢኮኖሚው መስክ ወደ አዲስ ምዕራፍ በመሸጋገር ላይ መሆኗን ተናግረዋል።

በአጠቃላይ ባለፉት ዓመታት በብዝኃ ዘርፍ ኢኮኖሚ ስርዓት፣ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ በማሳደግና አካታች ልማትን በመተግበር ብዙኃንን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል።

ለውጫዊና የሀገር ውስጥ ጫናዎች የማይበገር ኢኮኖሚ መገንባት የተቻለው መላውን ህዝብ በማሳተፍና በአመራሩ የተቀናጀ ጥረት መሆኑንም ተናግረዋል።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት ከተመዘገቡ ኢኮኖሚያዊ ስኬቶች መካከል የአገልግሎት የወጭ ንግድ የ9 ነጥብ 3 በመቶ እድገት በማስመዝገብ ትልቁን ድርሻ መያዙንም ገልጸዋል፡፡

ኢኮኖሚውን ከዳግም ስብራት ወደ ዕድገት ምህዋርነት በመቀየር በ2023 የሀገር ውስጥ ጥቅል ምርት ከ156 ቢሊዮን ዶላር በላይ ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል፡፡

በቀጣዮቹ ጊዜያት ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት፣ ሀገራዊ የቁጠባ ምጣኔን ለማሳደግ፣ ጤናማ የሆነ የመንግስት በጀት ጉድለትን በራስ አቅም ለመሸፈን እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡

የዋጋ ንረትን እና የኑሮ ውድነትን ማረጋጋት፣ የስራ አጥነት ችግሮችን ደረጃ በደረጃ መቅረፍ፣ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትን ለማሻሻልም ትልቅ ትኩረት እንደሚሰጥም እንዲሁ።

መንግሥት የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥን በማፋጠን እና የሀገር ውስጥ ገበያ ስርዓትን በማዘመን የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚን ለማረጋገጥ) ትኩረት እንደሚሰጥም ጠቁመዋል፡፡ 

ለዚህም ሀገራዊ የለውጥና የሰላም ትሩፋትን ማፅናት፣ መልሶ ግንባታን ማፋጠን፣ ስኬቶችን ማጠናከር እና ክፍተቶችን ማረም የመንግሥት ቀዳሚ ስራዎች ይሆናሉ ነው ያሉት። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም