በጅማ ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው ወደ ተግባር ተገብቷል

131

ጅማ ሰኔ 3 / 2015(ኢዜአ) ፡-  በጅማ ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት የግብርና  ምርታማነትን ለማሳደግ  የስድስት ዓመታት ፕሮጀክቶች ተቀርጸው  ወደ ተግባር መገባቱን ዩኒቨርሲቲው አስታወቀ።

የአፕል፣ የወተትና የበግ ስጋ ምርታማነትን ለማሳደግ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው ተግባራዊ መደረጉ ነው የተገለጸው።  

የደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ክላስተር ምክር ቤት በጅማ ዩኒቨርሲቲ የተጀመሩ ዘመናዊ የግብርና ፕሮጀክቶችን  አስመልክቶ ዛሬ ውይይት አካሄዷል።


 

ጅማ ዩኒቨርሲቲ  የሚያስተባብረው ይኸው ምክር ቤት ተቋማትን ለማቀናጀትና ግብርናውን ለማዘመን ብሎም ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ  ታልሞ መመስረቱ ይታወሳል።

በዩኒቨርሲቲው ግብርናና እንሰሳት ህክምና ኮሌጅ ዲን  ዶክተር ሰለሞን ቱሉ እንዳሉት፤ ምክር ቤቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ዘርፉን ለመደገፍ እንዲችሉና በቅንጅት ለመስራት እድል የፈጠረ ነው ብለዋል።

በዚህም ሶስት ዋና ዋና ፕሮጀክቶች ተቀርጸው በጅማ ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት በጅማ ዞን  በተመረጡ  አራት ወረዳዎች ለመተግበር ወደ ስራ መገባቱን አስታውቀዋል።

የአፕል፣ የወተትና የበግ ስጋ ምርታማነትን ለማሳደግ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው ተግባራዊ መደረጉን ተናግረዋል።  

በዴዶ ወረዳ  በተጀመረው የአፕል ፕሮጀክት 120  አርሶ አደሮች ችግኝ  እንዲተክሉ መደረጉንና በተጨማሪ  250 አርሶ አደሮችን ለማሳተፍ 10ሺህ ችግኝ ተዘጋጅቷል ብለዋል።

ሁለተኛው ፕሮጀክት የወተት ምርትን ለማሳደግ እንደሆነ አመልክተው፤ የተሻሻሉ የእንሰሳት ዝርያዎችን በማርባት 350 አርሶ አደሮች ተመርጠው አንድ ሺህ ላሞችን ለማዳቀል ዝግጅት ጨርሰናል ሲሉ ገልጸዋል።

በተሻሻለ ዝርያ የተመረጡ  ላሞች  የተለያዩ  የሳር ዝርያ ተመርጦ በዘጠኝ ሄክታር መሬት ላይ እየለማ መሆኑን አስረድተዋል።

ሶስተኛው ፕሮጀክት ደግሞ  የበግ ዝርያ በማሻሻል የስጋ አቅርቦትን ለመጨመር  ያለመ መሆኑን የተናገሩት ዲኑ፤ በዚህም 350 አርሶ አደሮችን በማሳተፍ እየተሰራ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

ለፕሮጀክቶቹ ማስፈጸሚያ 12 ሚሊዮን ብር ተመድቦ ለስድስት ዓመታት የሚቆይ ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግላቸው ያስታወቁት ዶክተር ሰለሞን፤ የዘርፉ ባለሙያዎችና አርሶ አደሮች በቅንጅት እንደሚፈጽሙት ተናግረዋል።

ዶክተር ሰለሞን እንዳመለከቱት፤ ፕሮጀክቶቹ በደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ በፍራፍሬና በወተት እንዲሁም በስጋ አቅርቦት ምርታማነትን በማሳደግ አርሶአደሩ የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆን ያግዛል።

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት  ፕሮፌሰር ነጻነት ወርቅነህ በበኩላቸው፤ በጥናትና ምርምር ተመስርተን የግብርውን ዘርፍ በማዘመን የምግብ ዋስትናን በአስተማማኝ ሁኔታ ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል።


 

የግብርናውን ዘርፍ ምርታማነት ለማሳደግ የዘርፉ ምሁራንና ተቋማትን ማደራጀት ብሎም የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን መደገፍና መከታተል እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።

የጅማ ዞን ከቡና ምርት በተጨማሪ በስንዴና በሩዝ ምርት ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን የገለጹት የጅማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ቲጃኒ ናስር ናቸው።


 

ዞኑ ከግብርና ምርምር ተቋማትና ከጅማ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ባለሙያዎች ጋር በመተባበር ውጤታማ የግብርና ስራ መስራቱንም አንስተዋል።

በዚህም  የተለያዩ ሰብሎችን አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የቡና ምርታማነት ማሳደግ እንደቻሉ ጠቅሰው፤  በምክር ቤቱ አማካኝነት መቀናጀታችን የበለጠ እንድንተባበር ያግዘናል ብለዋል።

በምክር ቤቱ ውይይት ላይ ከተለያዩ የግብርና ተቋማት የመጡ አመራሮችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም