ጫናን መቋቋም የሚችል ኢኮኖሚ ለመገንባት የታክስና ጉምሩክ ሕግ ተገዢነትን ማስፈን ይገባል - ገቢዎች ሚኒስቴር

183

ሀዋሳ ሰኔ 3/2015 (ኢዜአ)፡- ጠንካራና ጫናን መቋቋም የሚችል ሀገራዊ ኢኮኖሚ ለመገንባት የታክስና ጉምሩክ ሕግ ተገዢነትን ማረጋገጥ ከሁሉም ባለድርሻዎች የሚጠበቅ ኃላፊነት እንደሆነ የገቢዎች ሚኒስቴር ገለጸ። 

የደቡብ ክልል ግንባር ቀደም ግብር ከፋዮች የዕውቅናና ሽልማት መርሀ ግብር የክልልና የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት በቡታጅራ ከተማ ተካሂዷል።


 

በመርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት የገቢዎች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ ቱሉ የግብር ሥርዐቱን በማክበርና በማስከበር ጠንካራና ጫናን መቋቋም የሚችል ቀጣይነት ያለው ሀገራዊ ኢኮኖሚ መገንባት ይጠበቅብናል ብለዋል።

በመሆኑም ጠንካራ የታክስ ሥርዐትን መገንባትና የታክስና ጉምሩክ ሕግ ተገዢነትን ለማረጋገጥ ሁሉም ባለድርሻዎች በትኩረት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በሀገር ደረጃ ይህንን ለማሳካት የሚያስችል ከየካቲት 2015 ዓ.ም እስከ የካቲት 2016 ዓ.ም የሚቆይ የታክስና ጉምሩክ ሕግ ተገዢነት ንቅናቄ "ግብር ለሀገር ክብር" በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ እንደሚገኝ አስታውሰዋል።

የደቡብ ክልል ግንባር ቀደም ግብር ከፋዮችን ዕውቅናና ሽልማት የመስጠት መርሀግብርም የዚሁ ንቅናቄ አካል እንደሆነ ጠቅሰዋል።

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ከውጭ እርዳታና የኢኮኖሚ ጫና ተላቀን ሀገራችንን በራሳችን አቅም ማሳደግና ማልማት የምንችለው የውስጥ ገቢያችን ላይ በትኩረት መሥራት ስንችል ነው ብለዋል።


 

ለዚህም የተፈጥሮና የሰው ሀይል ፀጋዎችን ተጠቅሞ ኢኮኖሚን ማሳደግና ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሀብት ተገቢውን ግብር በአግባቡ መሰብሰብ ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት በክልሉ የተመዘገበውን የኢኮኖሚ ዕድገት በመጠቀም ገቢውን ማሳደግ እንደተቻለ ጠቅሰው፤ የክልሉ ገቢ ላለፉት አራት ዓመታት በአማካይ ከ30 በመቶ በላይ እያደገ መምጣቱን አስረድተዋል።

በትኩረትና በታማኝነት መስራት ከተቻለ ከዚህ በላይ ወጪውን መሸፈንና የልማት ሥራዎችን በአግባቡ ለመስራት የሚያስችል ገቢ መሰብሰብ እንደሚቻል ጠቁመዋል።

ግብር ከፋዩ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን በማሳደግ የተሻለ ገቢ ማስገኘት እንዲችል ከመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች ጀምሮ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር፣ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች በፍጥነት ወደ ሥራ ገብተው ገቢ ማመንጨት እንዲችሉ ማድረግና ገቢን በአግባቡ መሰብሰብ ከመንግስት አካላት የሚጠበቅ ተግባር እንደሆነ ገልፀዋል።

ግብር ከፋዮች የሚጠበቅባቸውን ግብር በታማኝነት መክፈላቸውን አጠናክረው በማስቀጠል በሀገራቸው ልማትና እድገት የበኩላቸውን አሻራ እንዲያኖሩ ጥሪ አቅርበዋል።


 

ከተሸላሚ ግብር ከፋይች መካከል በዲላ ከተማ በዱቄት ፋብሪካ፣ በቡና ንግድና ሌሎች ሥራዎች የተሰማሩት አቶ የሱፍ ጠሀ 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ግብር በመክፈል ተሸላሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

ለ14 ዓመታት ያህል ግብር በታማኝነት በመክፈል ሲሸለሙ መቆየታቸውን ጠቅሰው፤ መሸለሜ በመንግስትና ህዝብ ዘንድ ከማገኘው ክብርና ፍቅር ባሻገር ለሀገሬ እድገት የሚጠበቅብኝን በማድረጌ ደስተኛ ያደርገኛል ብለዋል።

ለሀገር የሚገባውን ግብር በታማኝነት መክፈል ጥቅሙ ለራስ እንደሆነም ተናግረዋል።

በመርሀግብሩ ላይ 58 ለታክስ ህግ ተገዢና ታማኝ የሆኑ ግንባር ቀደም ግለሰብ ግብር ከፋዮች፣ የመንግስት የልማት ድርጅቶች እና ሴክተር መስሪያ ቤቶች ዕውቅናና ሽልማት የተሰጣቸው ሲሆን ከ50 ሺህ 310 ብር እስከ 17 ሚሊዮን 914 ሺህ 763 ብር ድረስ ግብር የከፈሉ በደረጃ ሐ፣ ለ እና ሀ ግለሰብ ግብር ከፋዮች ተሸላሚ ሆነዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም