የሰላም በሮች ለሁሉም ክፍት መደረጋቸው በመላ አገሪቱ እየሰፈነ ላለው አንጻራዊ ሰላም መሠረት ሆኗል - የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ ሰኔ 3/2015(ኢዜአ)፡- የሰላም በሮች ለሁሉም ኃይሎች ክፍት መደረጋቸው  በመላ አገሪቱ እየሰፈነ ላለው አንጻራዊ ሰላም መሠረት መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ፤ በተለያዩ ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዩች ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። 

በመግለጫቸውም በአገሪቱ የሕግ የበላይነትን የማስፈንና ዘላቂ ሰላምን የማረጋገጥ እርምጃ የመንግሥት ቀዳሚ ተግባር ነው ብለዋል፡፡ 

ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ግጭትና ጦርነት የዜጎችን ደኅንነትንና ነፃነት አደጋ ላይ የሚጥሉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ሰላም በሌለበት ብልጽግና እንደማይረጋገጥ ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን የብልጽግና ተምሳሌት እንድትሆን  እየተሰራ መሆኑን  ተናግረዋል፡፡ 

አሁን እየተረጋገጠ ያለውን አንጻራዊ ሰላም ቀጣይነቱን ማረጋገጥና ቀዳሚ ተግባር መሆን እንዳለበትም ጠቅሰዋል፡፡

የሰላም በሮችን ለሁሉም ኃይሎች ክፍት ማድረግ መቻሉ በመላ አገሪቱ እየሰፈነ ላለው አንጻራዊ ሰላም መሠረት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የሰሜኑ ግጭት በፕሪቶሪያ እና በናይሮቢ ስምምነት መሠረት በተቀመጠለት አቅጣጫ በስኬታማነት እየተፈጸም እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በጋምቤላ ክልሎች የሚገኙ ታጣቂዎችም በተከፈተው የሰላም በር መጠቀም በመቻላቸው የተረጋጉ እና ሰላም የሰፈነባቸው ክልሎች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ከሸኔ ጋር የተጀመረው ሰላም የማስፈን ጥረትም ተጠናክሮ የሚቀጥል እንደሚሆንም ጠቁመዋል፡፡

 የአማራ ክልል አሁን ላይ ሰላም መሆኑን ገልጸው፤ በኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች ያሉትን ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ እንዲመለሱ በመደረጉ አብዛኞቹ መመለሳቸውን ገልጸዋል፡፡ 

አልፎ አልፎ ያፈነገጡትን ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከኅብረተሰቡ እና ከራሳቸው ጋር በተደረገ ውይይት አብዛኞቹ ወደ ቀደመው ህይወታቸው እንዲመለሱ መደረጉን ተናግረዋል፡፡  

 በዚህም ያልተመለሱት ላይ መንግሥት አስፈላጊ ያለውን ሕጋዊ እርምጃ መውሰዱን ጠቁመው፤ ይህ አሁንም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል፡፡

አሁን ላይ በአማራ ክልል  በተደረገው ውይይት  ሰላምና ጸጥታ እየሰፈነ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡  

 ዛሬም የኢትዮጵያን ሰላም የማይፈልጉ የውስጥና የውጭ ኃይሎች መኖራቸውን ጠቁመው፤ የተጀመረው ጠንካራ የሰላምና ደኅንነት ተቋም የመገንባት ሥራም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

   

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም