የተማርንበትን ትምህርት ቤት ለማዘመንና የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የሚደረገውን ጥረት ይበልጥ እናግዛለን- የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት የቀድሞ ተማሪዎች

አዲስ አበባ ሰኔ 3/2015(ኢዜአ)፡-  የቀድሞ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤትን ለማዘመንና የትምህርት ጥራቱን ለማስጠበቅ ለሚደረገው ጥረት  ያላሰለሰ ድጋፍ እንደሚያደርጉ የቀድሞ ተማሪዎች ገለጹ። 

በ1917 ዓ.ም. እንደተመሰረተ የሚነገርለት ፋና ወጊው የቀድሞ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት የአሁኑ ደግሞ የእንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ  ኮሌጅ አንድ ክፍለ ዘመኑን ሊደፍን ሁለት ዓመታት ብቻ ቀርተውታል። 

ትምህርት ቤቱ ለአገሪቱ የሥልጣኔ ጉዞ ትልቅ ሚና ማበርከቱን በርካቶች ይናገሩለታል። 

የትምህርት ቤቱ የቀድሞ ተማሪ አርቲስት ደበበ እሸቱ ትምህርት ቤቱ ለአገርና ለወገን የጠቀሙ በርካታ ምሁራንን አፍርቷል ብሏል። 

በየዘመኑ ከትምህርት ቤቱ የወጡ ሰዎች በተለያዩ ሙያ ዘርፎች ፈርጦች ሆነው አገራቸውን ማገልገላቸውን ገልፆ፤ ትምህርት ቤቱ እውቀትንና ክህሎትን ከማስጨበጥ ባለፈ ተማሪዎች በመልካም ሥነ-ምግባር ታንጸው እንዲወጡ በማድረግ ረገድ አስተዋጽዖ እንዳላቸው ተናግሯል።  

የትምህርት ቤቱ የቀድሞ ተማሪዎች ማኅበር በማቋቋም ትምህርት ቤቱን በተለያዩ ዘርፎች እየደገፉ እንደሚገኙ ገልፆ፤ ይህም ለትምህርት ጥራት መምጣት የራሱ የሆነ አበርክቶ ይኖረዋል ነው ያለው። 


 

ሌላኛው የትምህርት ቤቱ የቀድሞ ተማሪ ካፒቴን ከበደ ወልደፃዲቅ፤ ማኅበሩ ትምህርት ቤቱ የሚያስፈልጉትን አንዳንድ የትምህርት ቁሳቁስ መሣሪያዎችን ድጋፍ በማድረግ እገዛ እያደረገ እንደሚገኝ አንስተዋል። 

በተለይም ለመማር ማስተማር አገልግሎቱ ጠቀሜታ ያላቸውን የኮምፒውተር ክፍሎች ከማደራጀት ባለፈ በማዕድ ማጋራትና ለተማሪዎች አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን በማሟላት ለኮሌጁ እገዛ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል። 


 

አቶ ጋረደው አጥናፍ እና ሰዓሊ ሉዑልሰገድ ረታ የተባሉ የቀደሞ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች በበኩላቸው፤ ትምህርት ቤቱ በግብረገብነትና ሥነ-ምግባር አስተምህሮ  ላሉበት ደረጃ ያበቃቸው በመሆኑ አሁን ያለው ተተኪ ትውልድ በተመሳሳይ ለስኬት እንዲበቃ ትምህርት ቤቱን መርዳትና መደገፍ እንደሚገባ ተናግረዋል። 

በመሆኑም እነርሱ በትምህርት ቤቱ የትምህርት ጥራትን ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።


 

ትምህርት ለአንድ አገር እድገት ወሳኝ በመሆኑ የትምህርት ጥራትን ለማምጣት የተጀመረውን ሥራ ውጤታማ ለማድረግ የቀድሞ ተማሪዎች ያስተማራቸውን ትምህርት ቤት መርዳትና መደገፍ አለባቸው ሲል አርቲስት ደበበ እሸቱ ተናግሯል።

ካፒቴን ከበደ በበኩላቸው፤ የቀድሞ ተማሪዎች ያስተማራቸውን ትምህርት ቤት ተመልሰው በመደገፍ የትምህርት ጥራት እንዲመጣ አስተዋጽዖ ማድረግ እንደሚገባቸው ነው የተናገሩት። 

አቶ ጋረደው አጥናፍ እና ሰዓሊ ሉዑልሰገድ ረታ በበኩላቸው፤ የአገር እድገት መሠረት የሆኑትን ትምህርት ቤቶች መደገፍ የውዴታ ግዴታ መሆኑን ጠቁመዋል። 

በመሆኑም የቀድሞ ተማሪዎች ያስተማራቸውን ትምህርት ቤት በመደገፍ የትምህርት ጥራት እንዲጠበቅ ያላሰለስ ድጋፍ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።


 

የእንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን ተሾመ ፈይሳ በበኩላቸው፤ የትምህርት ቤቱ የቀድሞ ተማሪዎች ለመማር ማስተማሩ ከሚያደርጉት እገዛ ባሻገር ለተማሪዎች ሞራል ግንባታ አዎንታዊ አስተዋጽዖ እያበረከቱ እንደሚገኙ አንስተዋል። 

በመሆኑም ይህን ጥሩ ተሞክሮ በሁሉም ትምህርት ቤቶች በማስፋት የቀድሞ ተማሪዎች የተማሩበትን ትምህርት ቤት እንዲደግፉ በማድረግ የትምህርት ጥራትን ለማምጣት በሚደረገው ጥረት የራሳቸውን ጉልህ ሚና እንዲወጡ ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም