የተጀመረው የፍትህ ተቋማት የለውጥ ፍኖታ ካርታ ትግበራ በትኩረት ሊሰራ ይገባል--አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ 

193


ጅግጅጋ ሰኔ 3/2015(ኢዜአ)፦ ፍትህ ለሰላም፣ ለዘላቂ ልማትና ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ዋሳኝ ሚና ስላለው የተጀመረው የፍትህ ተቋማት የለውጥ ፍኖታ ካርታ ትግበራ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።

3ኛው ሀገር አቀፍ የህግ አውጪዎች የጋራ የምክክር መድረክ በጅግጅጋ ከተማ መካሄድ ጀምሯል። 


 

አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ እንደተናገሩት መድረኩ በመንግስታት መካከል ያለውን ግንኙነት ለመወሰን የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1231/2013 መሰረት በማድረግ በፌዴራል እና በክልሎች መካከል ያለ ግንኙነትን ለማጠናከር በየስድስት ወሩ የሚካሄድ መድረክ መሆኑን ገልጸዋል። 

ፍትህ ለማረጋገጥና ለማጠናከር በፌዴራል የፍትህ ተቋማት የተጀመረው የፍትህ የለውጥ ፍኖታ ካርታ በየደረጃው ያሉ የፍትህ ተቋማት ለመተግበር መስራት ይገባቸዋል ብለዋል። 

"ፍትህ ለሰላም፣ ለዘላቂ ልማት፣  ለፖለቲካና ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ወሳኝ ሚና አለው" ሲሉም አፈ-ጉባኤው ተናግረዋል።

በህግ አውጪዎች መካከል የሚደረገው ውይይት ዘላቂ ሰላምን በማስፈን፣ ዋስትና ያለው ዲሞክራሲ ለማረጋገጥ እና ፈጣን እድገት በማስመዝገብ፣ አንድ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመፍጠር ያግዛልም ብለዋል። 

የክልሎች እና የብሄረሰቦች ምክር ቤቶች እየተሳተፉበት በሚገኘው የምክክር መድረክም የእርስ በእርስ ግንኙነትን ከማጠናከር ባሻገር መልካም ተሞክሮዎች የሚለዋወጡበት እንደሆነም ጠቁመዋል። 

መድረኩ በፌዴራል ደረጃ በፍትህ ስርዓቱ ላይ የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎችን በክልሎችም ለማጠናከር የሚያግዝ ምክክር ይካሄድበታል ተብሏል። 

የሶማሌ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሁመድ፣ "እውነተኛ የዲሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት በየደረጃው የሚገኙ የፍትህ ተቋማት ተቋማዊ ነፃነታቸው ተጠብቆ በሰው ኃይል እና በቴክኖሎጂ ታግዘው መስራት ይጠበቅባቸዋል" ብለዋል። 


 

በሶማሌ ክልልም ከለውጡ በፊት የነበረ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለማስቀረት ሰፊ ስራዎች ተከናውነዋል፣ በዚህም ውጤቶች ታይተዋል ሲሉ ገልጸዋል። 

ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት በሚካሄደው መድረክ የፍትህ ተቋማት የለውጥ ፍኖታ ካርታ ስርዓት የጋራ ሰነድ እንዲሁም የፍርድ ቤቶች የአሰራር ለውጥ ላይ ያተኮረ ፍኖተ ካርታ ቀርቦ ውይይት እየተካሄደበት ይገኛል። 

በመድረኩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የፌደሬሽን ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሁመድ፣  የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት ቴዎድሮስ ምህረት፣ የፍትህ ሚኒስትር ዶክተር ጌድዮን ጢሞቲዎስ፣ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ እና የክልል፣ የሁለቱ ከተማ አስተዳደር እና የተለያዩ ብሄረሰቦች ምክር ቤቶች አፈ-ጉባኤዎች እና ምክትል አፈ-ጉባኤዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም