የኢትዮጵያ አየር ኃይልን ማዘመን የሚያስችሉ በርካታ የለውጥ ሥራዎች ተሰርተዋል - ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ

198


አዲስ አበባ ሰኔ 3/2015(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር ኃይልን ማዘመን የሚያስችሉ በርካታ የለውጥ ሥራዎች መሰራታቸውን የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ ተናገሩ።


በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አዘጋጅነት በቢሾፍቱ ከተማ በተካሄደው "የሥራ ባህልን መለወጥና የዕይታ አድማስን ማስፋት" የውይይት መድረክ የተሳተፉ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችና ሌሎች አካላት የአየር ኃይል የለውጥ ሥራዎችን ጎብኝተዋል።


 


የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ በተቋሙ የተወሰደው የለውጥ እርምጃ አገርን በችግር ውስጥም መገንባት እንደሚቻል ያሳየ ነው ብለዋል።


በኢትዮጵያ አየር ኃይልም አስተማማኝ የሰው ኃይልና ዘመናዊ ትጥቅ እንዲኖር በማድረግ እንዲሁም ተቋሙ ፅዱና ማራኪ እንዲሆን ያስቻለ የተለያዩ የለውጥ ሥራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል።


የሰራዊቱን አቅም በመገንባት ተቋሙንም ከማንኛውም የፖለቲካ፣ የኃይማኖትና የብሔር አስተሳሰብ ነፃና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኩራት እንዲሆን ማድረግ እንደተቻለም እንዲሁ። 


ኢትዮጵያ ታላቅ አገር ናት ያሉት ሌተናል ጄነራል ይልማ፤ አገሪቷም ያላትን ታሪክ፣ የቆዳ ስፋትና የሕዝብ ብዛት ታሳቢ በማድረግ በአየር ኃይል ላይ በርካታ የለውጥ ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል። 


በአየር ኃይል የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊና የ5ኛ አየር ምድብ አዛዥ ኮሎኔል ብሩክ ሰይፉ፤ ባለፉት ሦስት ዓመታት የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ዕቅድ በመንደፍ በተቋሙ ላይ ውጤታማ የልማት ሥራ ተሠርቷል ብለዋል።


በዚህም በሰው ኃይልና በዘመናዊ ትጥቅ በማደራጀት የኢትዮጵያን አየር ክልል ማስጠበቅ የሚያስችል አስተማማኝ ተቋም መገንባት እንደተቻለ ገልጸዋል።


የአየር ኃይልን ቅጥር ግቢ ውብና ማራኪ በማድረግ ምቹ የሥራ አካባቢን መፍጠር ያስቻለ ውጤታማ የልማት ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።


በጉብኝቱ የተሳተፉ አካላትም አየር ኃይል ባጠረ ጊዜ በሰው ኃይል፣ በዘመናዊ ትጥቅ ግንባታ፣ ተቋም የማስዋብና የማልማት ሥራ ላይ ያከናወናቸው ተግባራት አስደናቂ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 


ከጎብኝዎች መካከል አንዱ የሆኑት የዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት ዋና ሥራ አስፈጻሚ መሐመድ ሐሰን በሰው ኃይልና ተቋማዊ የለውጥ ማሻሻያ በማድረግ የተሻለ ቁመና ላይ እንዲገኝ መደረጉ አስደናቂ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም