መደበኛ ፖሊስን የተቀላቀሉ የቀድሞ ልዩ ሃይል አባላት ለፖሊስ አቅም መጠናከር የበኩላቸውን ሚና መጫወት አለባቸው - አቶ ደሳለኝ ጣሰው


ባህርዳር ሰኔ 03/2015(ኢዜአ)፦ መደበኛ ፖሊስን የተቀላቀሉ የቀድሞ ልዩ ሃይል አባላት ልምዳቸውንና እውቀታቸውን በመጠቀም ለፖሊስ አቅም መጠናከር የበኩላቸውን ሚና መጫወት እንዳለባቸው የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ገለጹ።

የክልሉ የቀድሞ ልዩ ሃይል አባላትን በተለያዩ የጸጥታ ዘርፎች መልሶ ለማደራጀት በተወሰደው እርምጃ የመደበኛ ፖሊስን የመረጡትን "ወንጀልን የመከላከል የመደበኛ ፖሊስ" ስልጠና በመውሰድ በዛሬው እለት ተመርቀዋል። 


 

የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ እንዳስታወሱት፤ በክልሎች የሚገኙ የልዩ ሃይል አባላትን ወደ ተለያዩ የጸጥታ መዋቅሮች ማካተት ያስፈለገው ጠንካራ አገራዊ የጸጥታ መዋቅር ለመገንባት ነው። 

የቀድሞ የአማራ ልዩ ሃይል አባላትንም እንደየ ምርጫቸው በመደበኛ፣ በማረሚያ ቤት፣ በአድማ ብተናና በፌደራል ፖሊስ እንዲሁም በመከላከያ ሰራዊት በማካተት የማደራጀት ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

ይህም የህዝቡን ደህንነት ማስጠበቅ የሚያስችል ወጥነት ያለውና ጠንካራ የጸጥታ መዋቅር መገንባት በማስፈለጉ መሆኑን አስረድተዋል። 

ጠንካራ የጸጥታ አካል እንዳይኖር የሚፈልጉ ሃይሎች የሃሰት ፕሮፓጋንዳ በማናፈስና ውዥንብር በመፍጠር ልዩ ሃይሉን ለመበተን ያሴሩት ሴራ ከሽፏል ብለዋል።

የወንጀል መከላከል ስልጠና ወስደው የመደበኛ ፖሊስን የተቀላቀሉ የቀድሞ ልዩ ሃይል አባላትም ልምዳቸውንና እውቀታቸውን በመጠቀም ለክልሉ ፖሊስ አቅም መጠናከር የበኩላቸውን ሚና መጫወት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደጀኔ ልመንህ በበኩላቸው ስልጠና የወሰዱ የዛሬ ተመራቂዎች የሚሰጣቸውን ፖሊሳዊ ተልእኮ በመወጣት ህዝባዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።


 

የቀድሞ የአማራ ልዩ ሀይል አባላት ፖሊስን መቀላቀላቸው ለክልሉ መደበኛ ፖሊስ ትልቅ አቅም ነው ብለዋል።

አባላቱ በስልጠናው ያገኙትን ተጨማሪ እውቀትና ክህሎት በመጠቀም ሰላምን በማስፈንና መረጋጋትን በመፍጠር ሚናቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

የክልሉን ሰላም የማይፈልጉ ሃይሎች የሚያሰራጩትን የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ወደ ጎን በመተው ፖሊሳዊ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ለመወጣት መዘጋጀት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።


በምረቃ ስነ-ስርአቱ ላይ የክልሉ የጸጥታ መዋቅር ከፍተኛ አመራሮች፣ የክልልና የዞን አካላት መሳተፋቸው ታውቋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም