የዓለም አይኖች ሁሉ ወደ ኢስታንቡል - ኢዜአ አማርኛ
የዓለም አይኖች ሁሉ ወደ ኢስታንቡል

የዓለም አይኖች ሁሉ ወደ ኢስታንቡል
አዲስ አበባ ሰኔ 3/2015(ኢዜአ):- የአውሮፓ እግር ኳስ ትልቁ ክብር ወደ እንግሊዝ ወይስ ወደ ጣልያን ያመራ ይሆን?
ማንችስተር ሲቲ ለመጀመሪያ ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን በእጁ ያስገባል? ወይስ ኢንተር ሚላን ለአራተኛ ጊዜ የዋንጫው ባለቤት ይሆናል?
ፔፔ ጋርዲዮላ ወይስ ሲሞኒ ኢንዛጊ? ኧርሊንግ ሃላንድ ወይስ ላውታሮ ማርቲኔዝ?
ከአምበሎቹ ኢልካይ ጉንዶጋን እና ሳሚር ሃንዳኖቪች ዋንጫዋን ማን ከፍ ያደርጋል?
75 ሺህ 145 ተመልካች በሚያስተናግደው አታቱርክ ኦሊምፒክ ስታዲየም ከምሽቱ 4 ሰአት በማንችስተር ሲቲ እና ኢንተር ሚላን መካከል የሚደረገው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ ለነዚህ ጥያቄዎች ሁሉ ምላሽ ይሰጣል።
የዋንጫው አሸናፊ ለሆነው ቡድን የ20 ሚሊዮን ዩሮ ሽልማት ይበረከትለታል።
ተጠባቂው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ የዓለምን የእግር ኳስ ቤተሰብ ለ90 ደቂቃ ከዛም ካለፈ ለ120 ደቂቃ ምናልባትም ከዛ በላይ ቀልብ እና ስሜት ይዞ ይቆያል።
የእንግሊዙ ማንችስተር ሲቲ ዛሬ የሚጫወተው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ለመጀመሪያ ጊዜ ለማንሳት ብቻ ሳይሆን በዓመቱ የሶስትዮሽ ዋንጫ ባለቤትነት ሕልሙን ለማሳካት ነው።
ሰማያዊዎቹ በዘንድሮው የውድድር ዓመት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ እና የኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫን አንስተዋል።
የፔፕ ጋርዲዮላው ማንችስተር ሲቲ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ በክለቡ ታሪክ ውስጥ ትልቁን እና ደጋፊዎቹ ለዓመታት የጓጉለትን ስኬት ማስመዝገብ ይችላል።
“የእግር ኳስ ሊቅ” እየተባለ የሚጠራው የ52 ዓመቱ ስፔናዊ አሰልጣኝ ዋንጫውን ካነሳ “የዓለማችን የምንጊዜም ምርጥ አሰልጣኞች” ዝርዝር ውስጥ ስሙን ማጻፍ ይችላል እያሉ ነው የእግር ኳስ ባለሙያዎቹ።
ጋርዲዮላ የስፔኑ ኃያል ክለብ ባርሴሎና አሰልጣኝ በነበረበት ወቅት ሁለት ጊዜ (እ.አ.አ 2008/09 እና 2010/11) የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን አንስቷል።
ማንችስተር ሲቲን ይዞ እ.አ.አ 2020/21 የሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ ቢደርስም በቼልሲ 1 ለ 0 መሸነፉ የሚታወስ ነው።
ማንችስተር ሲቲ በግማሽ ፍጻሜ የ14 ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊው ሪያል ማድሪድን በደርሶ መልስ 5 ለ 1 በማሸነፍ ለፍጻሜው ደርሷል።
ሲቲ በኢትሃድ ስታዲይም በተካሄደው የመልስ ጨዋታ ከጨዋታ ብልጫ ጋር 4 ለ 0 ያሸነፈበት ብቃት አድናቆትን ያስቸረው ነው። ያስመዘገበው ድል ዋንጫውን ያነሳል የሚል ግምትም አሰጥቶታል።
ማንችስተር ሲቲ በ2022/23 የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር እስካሁን ባደረጋቸው 12 ጨዋታዎች 31 ግቦችን ሲያስቆጥር 5 ግቦችን አስተናግዷል።
ካደረጋቸው ጨዋታዎች መካከል በሰባቱ ግብ አላስተናገደም።
በመጀመሪያው የውድድር ዓመት አስደናቂ ብቃት እያሳየ የሚገኘው የ22 ዓመቱ ኖርዌያዊ ኮከብ ኧርሊንግ ሃላንድ በሻምፒዮንስ ሊጉ በ10 ጨዋታዎች 12 ግቦችን በማስቆጠር የውድድሩ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነትን እየመራ ነው።
ወጣቱ አጥቂ በውድድር ዓመቱ በአጠቃላይ 52 ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፏል።
በማንችስተር ሲቲ የመጀመሪያውን የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ የማንሳት መንገድ ላይ የጣልያኑ አንጋፋ እና ኃያል ክለብ ኢንተር ሚላን ቆሟል።
በ47 ዓመቱ የጣልያን የቀድሞ ኮከብ አጥቂ ሲሞኒ ኢንዛጊ የሚሰለጥነው ኢንተር ሚላን በተመሳሳይ እንደ ማንችስተር ሲቲ በውድድር ዓመቱ ሶስተኛ ዋንጫውን ለማንሳት ይጫወታል።
ኔራዙሪዎቹ(ጥቁር እና ሰማያዊዎቹ) በዘንድሮው የውድድር ዓመት የጣልያን ጥሎ ማለፍ እና የጣልያን አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን አንስተዋል።
ኢንተር ሚላን ለአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ የደረሰው የከተማ ተቀናቃኙን ኤሲ ሚላንን በግማሽ ፍጻሜው በደርሶ መልስ 3 ለ 0 በማሸነፍ ነው።
የጣልያኑ ክለብ በዘንድሮው ዓመት የሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር 12 ጨዋታዎችን አድርጎ 19 ግቦችን ሲያስቆጥር 10 ጎሎችን አስተናግዷል።
አርጀንቲናዊው አጥቂ ላውታሮ ማርቲኔዝ እና ቤልጂየሚዊው የፊት መስመር ተጫዋች ሮሜሎ ሉካኩ እንዲሁም የአማካይ ተጫዋቹ ኒኮሎ ባሬላ በሻምፒዮንስ ሊጉ በተመሳሳይ ሶስት ግቦችን ለኢንተር ሚላን አስቆጥረዋል።
ላውታሮ ማርቲኔዝ በጣልያን ሴሪ አ 21 ግቦችን በማስቆጠር ናይጄሪያዊውን የናፖሊ አጥቂ ቪክቶር ኦሲሜን ተከትሎ በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ሁለተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።
አጠቃላይ በውድድር ዓመቱ 28 ግቦችን አስቆጥሯል።
ኢንተር ሚላን ከዚህ ቀደም የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ሶስት ጊዜ አንስቷል። (እ.አ.አ 1964፣ 1965 እና 2010)
ኢንተር ሚላን እ.አ.አ በ2010 የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ የደረሰው በግማሽ ፍጻሜው በወቅቱ በአሰልጣኝ ፔፔ ጋርዲዮላ ይመራ የነበረውን ባርሴሎናን በደርሶ መልስ ውጤት 3 ለ 2 በማሸነፍ ነበር።
በወቅቱ የኢንር ሚላን አሰልጣኝ የነበሩት ፖርቹጋላዊ አሰልጣኝ ጆዜ ሞውሪኒዮ ናቸው።
ማንችስተር ሲቲ እና ኢንተር ሚላን ከዚህ ቀደም በፉክክር ጨዋታዎች ላይ ተገናኝተው አያውቁም።
ከዚህ በፊት ሁለት ጊዜ የወዳጅነት ጨዋታ አድርገው አንድ አንድ ጊዜ ተሸናንፈዋል። (እ.አ.አ 2010 ኢንተር ሚላን እና እ.አ.አ 2011 ማንችስተር ሲቲ በተመሳሳይ 3 ለ 0 አሸንፈዋል)
የ42 ዓመቱ ፖላንዳዊ ዳኛ ሲሞን ማርሲኒያክ የተጠባቂው ጨዋታ የመሐል ሜዳ አለቃ ናቸው።
የዛሬውን ጨዋታ የሚያሸንፈው ክለብ ከዋንጫው በተጨማሪ የ20 ሚሊዮን ዩሮ ሽልማት ሲያገኝ ተሸናፊው ክለብ 15 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዩሮ የገንዘብ ሽልማት ይበረከትለታል።
የዓለም አይኖች ዛሬ ከምሽቱ 4 ሰአት ጀምሮ በአታቱርክ ኦሊምፒክ ስታዲየም ላይ ያርፋሉ።