በረሃማነትን ለመከላከል ዓለም አቀፍ ትብብር ያስፈልጋል-ዶክተር እንድርያስ ጌታ

265

አዲስ አበባ ሰኔ 3/2015(ኢዜአ):- በረሃማነትን ለመከላከል ዓለም አቀፍ ትብብር አስፈላጊ መሆኑን የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እንድርያስ ጌታ ገለጹ።

29ኛውን የዓለም በረሃማነትን የመከላከል ቀንን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀው ሶስተኛው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ትናንት በቻይና ተጀምሯል።

ጉባኤው በቻይና የሳይንስ አካዳሚ እና በአካዳሚው ሺንጂያንግ የኢኮሎጂ እና ጂኦግራፊ ኢንስቲትዩት አጋርነት የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።


 

በመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እንድርያስ ጌታ የተመራ ልዑክ በጉባኤው ላይ እየተሳተፈ ነው።

ሚኒስትር ዴኤታው በጉባኤው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር በረሃማነትን ለመከላከል ዓለም አቀፍ ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል።

ዶክተር እንድርያስ በጉባኤው በኢትዮጵያ ቆላማ አካባቢዎች በረሃማነትን ለመከላከል እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን ተሞክሮ አቅርበዋል።

ከፎረሙ ጎን ለጎን የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር በቻይና የሳይንስ አካዳሚ እና ሺንጂያንግ የኢኮሎጂ እና ጂኦግራፊ ኢንስቲትዩት በኢትዮጵያ ቆላማ አካባቢዎች በረሃማነትን መከላከል የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት እንደሚፈራረሙ ተገልጿል።

ዶክተር እንድሪያስ ከሲኖ አፍሪካ የጋራ ምርምር ማዕከል ኃላፊዎች ጋር በኢትዮጵያ እና በቻይና መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ይወያያሉ ተብሎም ይጠበቃል።

እስከ ሰኔ 15/2015 በሚቆየው ዓለም አቀፍ ፎረም ላይ የተለያዩ አገራት በረሃማነትን በመከላከል ረገድ ያላቸውን ተሞክሮዎች እንደሚያቀርቡ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባሰፈረው መረጃ አመልክቷል።

በተጨማሪም የተለያዩ አገራት ባለሙያዎች፣ ተመራማሪዎች እና ልዑካን ቻይና በረሃማነትን ለመከላከል በ “Takilmakan” በረሃ እያከናወነች ያለውን ስራ እንደሚጎበኙም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም