በመጀመሪያው አረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የተገኙ ስኬቶችን በሁለተኛው ምዕራፍ መድገም ይገባል--የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ ሰኔ 3/2015(ኢዜአ)፦ በመጀመሪያው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የተገኙ ስኬቶችን በሁለተኛው ምዕራፍ ለመድገም መረባረብ ይገባል ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

በቀጣዮቹ የክረምት ወራት የትምህርት ተቋማትን ለመማር ማስተማር ምቹ የማድረግ ስራ እንደሚሰራም አገልግሎቱ ገልጿል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ በተለያዩ ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዩች ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በመጀመሪያው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የተገኙ ስኬቶችን በሁለተኛው ምዕራፍ መድገም ይገባል ብለዋል።

በመጀመሪያው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ከ25 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ለሶስት ዓመታት በሚተገበረው የሁለተኛው ምዕራፍ መርሃ ግብርም 25 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ዕቅድ መያዙን ገልጸዋል።

ለዚህ ስኬትም ህዝቡ በመጀመሪያው ምዕራፍ ያሳየውን ርብርብ በተጠናከረ መልኩ መድገም ይገባዋል ብለዋል።

በተያያዘም በክረምቱ ወራት የትምህርት ተቋማትን ለመማር ማስተማር ስራው ምቹ የማድረግ ስራ እንደሚሰራም ገልጸዋል።

ንቅናቄው በቅርቡ ይፋ የሚደረግ መሆኑን ጠቁመው፤ ለንቅናቄው ስኬታማ መሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊረባረቡ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

በክረምቱ ወራት በሚከናወነው የመኸር እርሻ አንድም መሬት ጦም እንዳያድር በመሰራት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

በከተሞች አካባቢ የከተማ ግብርናን ማስፋት እንደሚገባም ገልጸዋል።

የሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በተገኙበት "ነገን ዛሬ እንትከል" በሚል መሪ ሃሳብ በአፋር ክልል መጀመሩ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም