የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከራሱ በፊት ለህዝብና ለሃገር ጥቅም መቆም ቀዳሚውና ዋነኛው እሴቱ ነው--መከላከያ ሚኒስቴር

224

አዲስ አበባ ሰኔ 03/2015(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ቁልፍ እሴት ከሆኑት ቀዳሚውና ዋናው ከራስ በፊት ለህዝብና ለሃገር ጥቅም መቆም መሆኑን መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ዩኤስኤአይዲ (USAID) ሰሞኑን አጣርቻለሁ ብሎ ባወጣው መግለጫ ለሰብአዊ እርዳታ የመጣን እህል ከሌሎች መንግስታዊ አካላት ጋር በመሆን መከላከያ ሰራዊታችንም እንደተጠቀመ አድርጎ ያቀረበውን ሪፖርት የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሲዘግቡት አስተውለናል ብሏል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በጥብቅ ዲሲፕሊን የሚመራና ዘመናዊ መሆኑን የገለጸው ሚኒስቴሩ ሰብዓዊ ድጋፍ የሚደረግላቸውን ወገኖቹን ቀለብ ሊቀማ ቀርቶ፤ ከቀለቡ ቀንሶ የሚያካፍል ሰራዊት መሆኑን የሃገሩ ዜጎች ብቻ ሳይሆኑ በአጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሰላም ማስከበር በተሰማራባቸው ቦታዎች ሁሉ የተመሰከረለት መሆኑን ገልጿል።

ኢትዮጵያ ለሰራዊቷ ደመወዝና ቀለብ መስጠት በመጀመር ቀዳሚ ነን ከሚሉ ሃገራት ተርታ የምትሰለፍ ነፃ እና ታሪካዊት ሃገር መሆኗን በመግለጫው የጠቀሰው የመከላከያ ሚኒስቴር የሰራዊቱ ቀለብ ለሃገር ውስጥ ነጋዴዎች እድሉን በመስጠት በግልፅ ጨረታ ተወዳድረው ስንዴም ሆነ ሌሎች ምግብ ነክ ፍጆታዎች የሚቀርብለት በተሟላ አሰራር የሚመራ ሰራዊት ነው ብሏል።

ዩኤስኤአይዲ በሠጠው መግለጫ መሠረት ምናልባት የመከላከያ አባል የሆነ ወታደር በማይመለከተው ገብቶ ከመዋቅር ውጪ ሕግ የማስከበር ሥራውን ተጠቅሞ ከሌቦች ጋር በመተባበር እርዳታ ተሰርቆ እንዲወጣ በግል የተባበረ ካለ እና ተጣርቶ ከተገኘ የአገር መከላከያ ሠራዊት አመራር የማያዳግም እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቋል።

መከላከያ ሚኒስቴር ያወጣው መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦

ከኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር የተሰጠ መግለጫ

ሰኔ 03/2015 ዓ.ም

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ቁልፍ እሴት ከሆኑት ቀዳሚውና ዋናው ከራስ በፊት ለህዝብና ለሃገር ጥቅም መቆም ነው፡፡

ዩኤስኤአይዲ (USAID) ሰሞኑን አጣርቻለሁ ብሎ ባወጣው መግለጫ ለሰብአዊ እርዳታ የመጣን እህል ከሌሎች መንግስታዊ አካላት ጋር በመሆን መከላከያ ሰራዊታችንም እንደተጠቀመ አድርጎ ያቀረበውን ሪፖርት የተለያዩ ሚዲያዎች ሲዘግቡት አስተውለናል፡፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በጥብቅ ዲሲፕሊን የሚመራ ዘመናዊ ሰራዊት ነው፡፡ ሰብዓዊ ድጋፍ የሚደረግላቸውን ወገኖቹን ቀለብ ሊቀማ ቀርቶ፤ ከቀለቡ ቀንሶ የሚያካፍል ሰራዊት መሆኑን የሃገሩ ዜጎች ብቻ ሳይሆኑ በአጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሰላም ማስከበር በተሰማራባቸው ቦታዎች ሁሉ የዕለት ከዕለት ተግባሩ መሆኑን የደረሰላቸው ህዝቦች፤ መንግስታት እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሁሉ የሚያውቁት ሰመ ጥር ህዝባዊ ሰራዊት ነው፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ ለሰራዊቷ ደመወዝና ቀለብ መስጠት ከጀመረች፤ ቀዳሚ ነን ከሚሉ ሃገራት ተርታ የምትሰለፍ ነፃ እና ታሪካዊት ሃገር ናት፡፡

ሰራዊታችን ዘመናዊ ነው ከሚያስብሉት አንዱ ደግሞ ይኸው ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው የሎጂስቲክ ግዥ እና አቅርቦት ጉዳይ ነው፡፡ የሰራዊታችን ቀለብ ለሃገር ውስጥ ነጋዴዎች እድሉን በመስጠት በግልፅ ጨረታ ተወዳድረው ስንዴም ሆነ ሌሎች ምግብ ነክ ፍጆታዎች የሚቀርብለት በተሟላ አሰራር እና አመራር የሚመራ ሰራዊት ነው፡፡

የኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት፡-

1ኛ/ ሠራዊታችን በቂ ሎጄስቲክ ያለው በዓለም አቀፍና በአገር ውስጥ ለተፈናቀሉትና በድርቅ ለተጎዱት በዓይነትና በገንዘብ የሚረዳ እንጂ ተቸግሮ ከአሰራር ውጭ የሚጠቀም አይደለም።

2ኛ/ ሠራዊታችን ማንኛውንም ዓይነት ምግብ በበጀቱ በሕግና በግልፅ ጨረታ ገዝቶ የሚጠቀም እንጂ ተቸግሮ የሕዝብ እርዳታ አካባቢ ሄዶ እርዳታ ላይ የሚሻኮትበት ዓይነት ድህነት የለበትም። ጥቆማ የሰጠ አካል እንኳ ቢኖር እስኪጣራ ሳይጠበቅ፤ እንደ ተቋምና እንደ ሠራዊት ስም የሚያጠፋ የሚዲያ ሽፋን መስጠት የኢትዮጵያን መከላከያ ሠራዊት ክብር ይነካል።

3ኛ/ ምንም እንኳን አገራችን በሚሊዮን የሚቆጠር እርዳታ ጠባቂ ሕዝብ ቢኖራትም ሠራዊቷን መመገብ የምትችልና በቂ ምግብና በጄት በመመደብ ሠራዊቱ ራሱ በሕግና በተቋም ሎጂስትክ አማካኝነት የምትመግብ አገር ናት። ሠራዊታችንም ኩሩና የችግረኞችን ስንዴ የማይሻማ ፕሮፌሽናል ሠራዊት ነው። ስለሆነም የእርዳታ ስንዴ የሚጠቀም ተቋም ወይም ዩኒት ወይም ወታደር የለንም።

4ኛ/ ዩኤስኤአይዲ (USAID) በሠጠው መግለጫ መሠረት ምናልባት የመከላከያ አባል የሆነ ወታደር በማይመለከተው ገብቶ ከመዋቅር ውጪ ሕግ የማስከበር ሥራውን ተጠቅሞ ከሌቦች ጋር በመተባበር እርዳታ ተሰርቆ እንዲወጣ በግል የተባበረ ካለ እና ተጣርቶ ከተገኘ የአገር መከላከያ ሠራዊት አመራር የማያዳግም እርምጃ ይወስዳል።

መከላከያ ሰራዊት ለሃገሩም ሆነ ለዓለም አቀፍ ሰላም መከበር መሰዋትነት የሚከፍል ምስጉን ሰራዊት ሆኖ እያለ፤ በአገራችን ውስጥና በውጪ አገር ያሉ ጥቂት የአገር መከላከያ ሠራዊት ጥላቻ ያላችው ፅንፈኞች እንዳሉ እናውቃለን። መካላከያን የማጠልሸት ሥራ የቆየና የለመድነው ነው።

የመከላከያ ሠራዊታችንን ህዝባዊ ተፈጥሮ፣ አሰራርና ሥርዓት ሳይታወቅና መረጃ እንኳ ቢመጣ፤ አጣርቶ ሳይታወቅ፤ መረጃ የቀረበበት አካል ሳይጠየቅ፤ የሚዲያ ሽፋን መሰጠት ትክክል አይደለም ብለን እናምናለን። የሚመለከታቸው የእርዳታ ሰጪ ድርጅቶችና የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲያጣሩ እንተባበራለን። ከተጣራ በኋላ ሁሉንም ለሕዝብ ይፋ እናደርጋለን።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም