በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ካለፈው ዓመት የዞረውን ጨምሮ 6 ሺህ 269 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ቀርቧል

ሰቆጣ ሰኔ 03/2015 (ኢዜአ) በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር 6 ሺህ 269 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ መቅረቡን የአስተዳደሩ ግብርና መምሪያ አስታወቀ። 

የቀረበው የአፈር ማዳበሪያ ከፍላጎቱ አንጻር ሰፊ ክፍተት ያለበት በመሆኑ የተፈጥሮ ማዳበሪያን በአማራጭነት አርሶ አደሩ እንዲጠቀም ተጠይቋል።

የመምሪያው ሃላፊ አቶ አዲስ ወልዴ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በብሄረሰብ አስተዳደሩ ለመጪው የምርት ዘመን 19 ሺህ 560 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በመጠቀም ምርታማነትን ለማሳደግ ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል። 

በክልሉ በሚስተዋለው ማዳበሪያ እጥረት ለመፍታት  11 ሺህ 148 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እንደሚቀርብ የተገለጸ ቢሆንም እስካሁን የቀረበው 3 ሺህ 359 ኩንታል ብቻ መሆኑ አሳሳቢ ነው ብለዋል። 

ችግሩን ለመፍታት በተደረገው ጥረት ካለፈው ዓመት የዞረውን ጨምሮ 6 ሺህ 269 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ማሰራጨት መቻሉን ተናግረዋል። 

አርሶ አደሮች እስከ ሶስት ጊዜ መሬቱን ደጋግመው በማረስ ያዘጋጁ ቢሆንም የአፈር ማዳበሪያ እጥረት የእርሻ ስራውን እንዳያስተጓጉልባቸው መስጋታቸውን አመልክተዋል።

ለክልሉ በቅርቡ ከሚገባው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ ለብሄረሰብ አስተዳደሩ ሲደርስ ለአርሶ አደሩ በፍጥነት በማሰራጨት ዘሩን እንዲዘራ እንደሚደረግ አስረድተዋል። 

ከዚህ በተጨማሪም ያጋጠመውን የማዳበሪያ እጥረት አርሶ አደሩ ተገንዝቦ ባለፈው በጋ ያዘጋጀውን 733 ሺህ ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በአግባቡ ተጠቅሞ እንዲዘራ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።

የተዘጋጀው የተፈጥሮ ማዳበሪያም 120 ሺህ ሄክታር መሬት መሸፈን የሚችል መሆኑን ጠቁመው፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ፈጥነው የሚበሰብሱ እጸዋቶችንና ፍግን በመጠቀም ተጨማሪ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት እንዲጠቀሙ መክረዋል።


 

የብሄረሰብ አስተዳደሩ ምክትል አስተዳዳሪና የኢንቨስትመንት መምሪያ ሃላፊ አቶ ሹመት ጥላሁን የተከሰተውን የማዳበሪያ እጥረት ለመቅረፍ አርሶ አደሩ የተፈጥሮ ማዳበሪያ መጠቀም እንዳለበት አስገንዝበዋል። 

በጋዝጊብላ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ወዳጅ ጌታሁን እንዳሉት፤ የማዳበሪያ አቅርቦት ችግር በመኖሩ በግብርና ስራቸው ላይ መስተጓጎል ገጥሟቸዋል።

የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ በማቅረብ የመኸር እርሻቸውን በወቅቱ እንዲያከናውኑ የሚያስችል ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።

በሰቆጣ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር በሩ ፈንታ በበኩላቸው ማሳቸውን በአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት ምክንያት ማረስ እንዳልቻሉ ተናግረዋል።  

በብሄረሰብ አስተዳደሩ በ2015/16 የምርት ዘመን ከ120 ሺህ 638  ሄክታር መሬት በሰብል በመሸፈን ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን የመምሪያው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም