በትግራይ ክልል ከተሞችን መልሶ ለመገንባት የፌደራል መንግስት ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር ለመስራት መንቀሳቀስ ጀምሯል- ሚኒስቴሩ

መቀሌ  ሰኔ 3 / 2015(ኢዜአ) ፡- በትግራይ ክልል በነበረው ችግር ጉዳት የደረሰባቸውን ከተሞች መልሶ ለመገንባት ከአለም ባንክና ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር  በቅንጅት ለመስራት እንቅስቃሴ  መጀመሩን  የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ገለጸ።  

ሚኒስቴሩ ከተባባሪ አካላት ጋር በመሆን  በከተሞች መልሶ ግንባታ፤በወጣቶችና ሴቶች  ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ላይ  ከክልሉ ለተወጣጡ የከተማ ልማት አመራሮችና ባለሙያዎች በመቀሌ ከተማ ያዘጋጀው ስልጠና ተጀምሯል።


 

በስልጠናው መድረክ ላይ የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የከተማ ልማትና ቤቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሄለን ደበበ እንዳሉት፤  በነበረው ችግር በትግራይ ክልል ጉዳት ከደረሰባቸው አንዱ  የከተማ መሰረተ ልማት ነው።

ጉዳት የደረሰባቸውን ከተሞች መልሶ በመገንባት በዘርፉ የወጣቶችና ሴቶች ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የፌዴራል መንግስት ከዓለም ባንክና ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር ተቀናጅቶ ለመስራት መንቀሳቀስ ጀምሯል ብለዋል።

በትግራይ ክልል  ጉዳት የደረሰባቸውን ከተሞች  መልሶ ለመገንባት በሚደረገው እንቅስቃሴ በየከተማው የተመደቡ አመራሮችና ባለሙያዎች የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸው አመልክተዋል።

የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የከተማ መሰረተ ልማት ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ አልማዝ ገብረፃዲቅ በበኩላቸው፤ የተጎዱ ከተሞችን መልሶ በማቋቋም የህዝቡን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ  በሚደረገው ጥረት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር  ከፌዴራል መንግስት ጋር ተቀናጅቶ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን አስታውቀዋል።


 

በመቀሌ በተዘጋጀው የሶስት ቀናት ስልጠና ላይ ከትግራይ ክልል ዘጠኝ ከተሞች የተውጣጡ ከ100 የሚበልጡ የከተማ ልማት ዘርፍ አመራሮችና ባለሙያዎች በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙ ኢዜአ ከሥፍራው ዘግቧል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም