11ኛው የቱሪዝም ጥናትና ምርምር ጉባኤ በጂንካ ከተማ እየተካሄደ ነው

ጂንካ ሰኔ 3/2015(ኢዜአ)፦ በቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩትና በጂንካ ዩኒቨርሲቲ ትብብር የተዘጋጀው 11ኛው ዓመታዊ የቱሪዝም ጥናትና ምርምር ጉባኤ በጂንካ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የዘንድሮው የቱሪዝም ዓመታዊ የጥናትና ምርምር ጉባኤ "ብዝሃነትና ዘላቂ የቱሪዝም ልማት ለስራ እድል ፈጠራ'' በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ይገኛል።


 

የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ እንደተናገሩት፤ ኢንስቲትዩቱ በቱሪዝም ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል።

በቱሪዝም መስክ ያለውን እምቅ ሀብት ጥቅም ላይ ለማዋል ጥራቱን የጠበቀ የክህሎት ስልጠና መስጠት እንደሚገባ ገልጸዋል።

''የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የሰለጠነና የበቃ የሰው ሃይል ይፈልጋል'' ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የሰው ሀይሉን በስልጠና በማብቃትና በቴክኖሎጂ በማገዝ ዘርፉን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ኩሴ ጉድሼ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የብዝሃ-ባህልና የቱሪዝም መስኩን እንደ አንድ የልህቀት ማዕከል አድርጎ በመሥራት ላይ ይገኛል ብለዋል።

በጉባኤው ላይ የሚቀርቡ የጥናትና ምርምር ውጤቶችም ዩኒቨርሲቲው በቱሪዝም መስክ ለሚያከናውናቸው ሥራዎች አጋዥ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

በጉባኤው “በቱሪዝም መስክ ያሉ እድሎችና ፈተናዎች”እንዲሁም “የክህሎት ስልጠና ለዘላቂ የቱሪዝም እድገት” በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር ይደረጋል።

የፌዴራልና የክልል የዘርፉ አስፈጻሚዎችና ባለድርሻ አካላት፣ የሆቴልና ቱሪዝም ድርጅቶች፣ የትምህርት ስልጠና ተቋማትና የሙያ ማህበራት ተወካዮች በጉባኤው ላይ ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም